
ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጤና ተቋማት በትኩረት እየተገነቡ ይገኛሉ። በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በ2010 ዓ.ም የተጀመረው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደባይ ጥላት ግን ወረዳ የሚገኘው የቁይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አንዱ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያም ይህን ሆስፒታል የግንባታ አፈጻጸም በተመለከተ መጋቢት ወር መዘገቡ ይታወሳል።
የቁይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ በ2010 ዓ.ም ከ297 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት በአቢታ ኮንስትራክሽን ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ በቁሳቁስ የዋጋ ንረት ምክንያት ግንባታው ተቋርጦ ቆይቷል።
ሆስፒታሉ እንደገና መቅደላ ኮንስትራክሽን ውል ይዞ እየሠራው መኾኑንም አሚኮ ከዚህ በፊት ዘግባል።
በመቅደላ ኮንስትራክሽን የቁይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ኘሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ ባዬ ገጥአለ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ መቅደላ ኮንስትራክሽን ግንባታውን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል መያዙን አስታውሰዋል። ነገር ግን በክልሉ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ሥራው እንደገና ተስተጓጉሎ እንደነበር አንስተዋል። ከታኅሣሥ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ግን ችግሩን በመቋቋም የግንባታ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ እንደገለጹት በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት ግንባታው መቶ በመቶ መጠናቀቁን አንስተዋል።
ለማኅበረሰቡ ለማስረከብ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ለአገልግሎት ሥራ ሲጀምር ከ100 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኅብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ የሚመልስ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
