
በትግራይ የሚደረገውን የወጣቶች አፈሳ እና የጦርነት ጉሰማ የሚቃወም የክልሉ ተወላጆች ሰልፍ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ሰልፈኞቹ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የጦርነት ዝግጅት እና የወጣቶችን አፈሳ ተቃውመዋል። ቡድኑ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን የግንኙነት መስመር በጥሶ ወጣቶችን እያሳደደ እና እያፈናቀለ ይገኛልም ነው ያሉት።
የፒሪቶሪያ ስምምነት እንዲከበር እና የፌዴራል መንግሥት የክልሉን ሕዝብ የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ችግሩን እንዲፈታም በሰልፉ ተጠቁሟል።
ሕገወጡ ሕወሃት እየጣሰ ያለው የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲከበር፤ አፈና ግድያ እና እንግልት እንዲቆም የክልሉ ተወላጆች ጠይቀዋል።
በዕለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሕገወጡ ሕወሃት ቡድን በክልሉ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር እንዲያስቆሙ ለፌዴራል መንግሥት እና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሕገወጡ ሕወሃት ቡድን እየተፈጸመ ያለውን አፈና እና ግፍ ለመቃወም የተዘጋጀ ሰላማዊ ሰልፍ መኾኑንም አስረድተዋል።
አሁንም ከጦርነት ውጭ መኖር የማይችለው ቡድን የተለያዩ ሴራዎችን እና የተዛቡ ወሬዎችን እያሰራጨ ቢኾንም፣ የሚሰማው ማንም የለም ብለዋል።
የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ዋና ዓላማ ጦርነቱ እንዲቆም፣ በወጣቶች ላይ የሚፈጸመው አፈና እንዲቀር እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ አሁንም በመፈናቀል ውስጥ
እንደሚገኝ ለማሳየት መኾኑን ገልጸዋል።
ይህ አፋኝ ቡድን ያለማቋረጥ ብዙ ወጣቶችን እየሠበሠበ ለጦርነት እየላከ፣ እየገደለ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሕይወት እያሳጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን እያፈረሰ እና ካፈረሰም በኋላ የተለያዩ ሴራዎችን እየሠራ በመኾኑ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ለዓለም ድምጽ ለማሰማት እንደኾነ ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የፌዴራል መንግሥት ብዙ ርቀት ቢጓዝም ይህ ቡድን ግን የተደረጉትን ጥረቶች ለማደናቀፍ መሰናክሎችን እየፈጠረ በመኾኑ ድምጻችንን ለዓለም እናሰማ ብለዋል።
ቡድኑ ከውጭ ኀይሎች ጋር በመተባበር የትግራይን ሕዝብ ወደማይፈልገው ቀውስ እየመራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት የትግራይ ሕዝብ ወደ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመለስ የፌዴራል መንግሥት እና የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሚገባቸውን ኀላፊነት በተገቢው ሁኔታ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
#አሚኮ #ሕገወጡ_የሕወሃት_ቡድን_እኩይ_ተግባር
#አዲስ_አበባ፡ሐምሌ11/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
