
🇪🇹ኢትዮጵያ በልጆቿ ክብር እና ፍቅር የታነጸች፣ በታሪክ አውድማ ላይ ስሟ በወርቅ ቀለም የተጻፈ ሀገር ናት። የውጭ ሀገር ፀሐፊዎች ሳይቀሩ ታሪኳን በብዕራቸው ሲከትቡት የኖሩት፣ አያሌ የጀግንነት ገድሏን በመመስከር ነው።
በዘመናት ውስጥ ሀገርን ለመውረር የውጭ ወራሪዎችም ኾኑ የውስጥ ከዳተኞች በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ሀገሪቱ በልጆቿ ጽናት አሳፍራ መልሳቸዋለች። ይህ ሁሉ ድል የተገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳት በአንድነት እና በሀገር ወዳድነት ስሜት ጠላትን በመመከታቸው ነው። የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተከፈለው መስዋዕትነት፣ ዛሬ ለምናያት ኢትዮጵያ መሠረት ኾኗል።
በየዘመናቱም ቢኾን የውጭ ጠላት ሲመጣ የሀገር ውስጥ ባንዳዎች መኖር ባዕድ አልነበረም፤ ነገር ግን በሕዝቡ የተባበረ ክንድ እና በጽኑ ጀግንነት የጠላት ህልም ሁሉ ከንቱ ኾኖ ቀርቷል።
በአሁኑ ወቅትም በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ከሕወሃት እና ከሌሎች የውጭ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ መኾናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ይህ ተግባር ለሕዝብ እቆረቆራለሁ ከሚል ወገን የማይጠበቅ እና የራስን ጥቅም ለማስቀደም ሲባል የሚፈጸም ታሪካዊ ክህደት ነው።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አበራ ታደሰ ባለፉት ሦሥት ዓመታት የአማራ ክልል የግጭት ቀጣና ውስጥ ነው ብለዋል። አኹን ላይ ደግሞ በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ የሕወሃት ቡድን ጋር ጥምረት በመፍጠር የጦርነት ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ዘወትር በተቃራኒ ከሚቆሙ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየፈጠሩ ይገኛሉ ነው ያሉት። ይህም ሁኔታ ለአማራ ክልል እጅግ ፈታኝ መኾኑን ነው ያስረዱት።
ይህ ከውጭ እና ከሕገ ወጡ ሕወሃት ቡድን ጋር በጋራ እየተፈጠረ ያለው ግጭትን የሚያባብስ ድርጊት በችግር እና በቀውስ ውስጥ የሚገኘውን የክልሉን ሕዝብ ዳግም ወደ ከፋ አዘቅት የሚከት መኾኑንም ነው የተናገሩት። ክልሉን የጦርነት አውድማ የሚያደርግም ነው ብለዋል።
መምህሩ እንደተናገሩት የራሳቸውን ዓላማ ብቻ ለማስፈጸም የሚፈልጉት እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች ጦርነቱ በአማራ ክልል እንዲካሄድ የሚፈልጉት መሠረተ ልማት እንዲወድም፣ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ እና የሕዝብ ንብረት እንዲወድም ካላቸው ፍላጎት የመነጨ መኾኑን ነው የገለጹት።
የዚህ የጥፋት ቡድን ጉዳት በአማራ ክልል ብቻ የሚወሰን ሳይኾን እንደ ሀገር አደገኛ አካሄድ ነው ይላሉ። ሀገሪቱን ወደ ኋላ የሚጎትት በመኾኑ በንቃት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ይህ ተግባር “ለአማራ ክልል ሕዝብ ነው የቆምኩት” የሚለውን ታጣቂ ቡድን ክህደትና እስከአሁንም ለግል ጥቅሙ በአማራ ሕዝብ ሲነግድ መቆየቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። ሕዝቡም እነዚህን አካላት መረጃዎችን በንቃት በመከታተል፣ በማጋለጥ እና በማውገዝ ሊታገላቸው ይገባል ነው ያሉት።
“ጦርነት ይብቃ፣ የሰው ሕይወት ከሞት ይዳን፣ የሀገር ደኅንነት እና ህልውና መጠበቅ አለበት” በሚል መርህ ሕዝቡ በአንድነት በመቆም እነዚህን ሀገወጥ ቡድኖች ሊያወግዝ እና ሊታገል እንደሚገባም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የሀገርን ሰላም በማስቀደም በውይይት መፍትሄዎችን መፈለግ የሁሉም ኅላፊነት ሊኾን ይገባልም ነው ያሉት። 🕊️
#ኢትዮጵያ #Peace #ጦርነትይብቃ
#ባሕር_ዳር፡ሐምሌ11/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
