በአዲስ አበባ 24 ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያዎች ዛሬ ሥራ ጀምረዋል፡፡

3
አዲስ አበባ: ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ ያስገነባቸውን 24 ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ወደ ሥራ አስገብቷል።
የኀይል መሙያ ጣቢያው ከኢንዲስት ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ጋር በመተባበር ነው የተገነባው።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ድኤታ በርሆ ሃሰን ኢትዮጵያ ተለዋዋጩን የዓለም የኀይል አቅርቦት አስቀድሞ በመገንዘብ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ እየተከተለች ትገኛለች ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የኤሌክትሪክ መኪኖች ኀይል መሙያ ከጥገኛ የኀይል አማራጭ አካባቢን ወደ ማይበክል ሉዓላዊ የኀይል አቅም ለመሻገር ሀገሪቱ እየተጓዘችበት ላለው ስትራቴጂ ስኬታማነት ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዜጎቿ ከበካይ የኀይል አማራጭ ነፃ የኾነ የትራንስፖርት አማራጮችን የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየሠራች ነው፤ ለዘርፉ ስኬታማነትም አስፈላጊው ድጋፎች ይደረጋሉ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው ውጤታማነት እና የደንበኛን እርካታ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን ተቋሙ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዛሬ ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡት ተቋሙ ከመጋቢት/2018 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያው ምዕራፍ እያስገነባቸው ከሚገኙ 40 ጣቢያዎች መካከል ናቸው። ጣቢያዎቹ በፍጥነት እና በቅናሽ ዋጋ የመኪኖችን ኀይል መሙላት እንደሚችሉም ተነግሯል።
በቀጣይም ሌሎቹ በሁለተኛው ምዕራፍ በኢትዮ ጅቡቲ ኮሪደር፣ ከቢሾፍቱ እስከ ሀዋሳ እና በየክልል ከተሞች ግንባታቸው በፍጥነት እንደሚከናወን ዋና ሥራ አሥፈፃሚው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ.ር) ወደ ሥራ የገቡት የኀይል መሙያዎች በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ በማድግ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ስኬታማ ለማድረግ ያግዛሉ ብለዋል።
በፓርኩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለመገጣጠም ወደ ሥራ እየገቡ ላሉ አልሚዎች እና ሌሎች አልሚዎች የስበት ማዕከል በመኾን ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ስኬታማነት አጋዥ ናቸው ብለዋል።
ዘጋቢ፡-ኢብራሂም መሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል ለ2018 ዓ.ም
Next articleየሀረሪ ክልል አሥተዳደር ምክር ቤት የቀረበለትን የበጀት ክለሳ አጸደቀ።