
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የጸጥታ ችግሩ ካጋጠመ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት የሰላም ጥሪዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፤ እያቀረበም ይገኛል።
ይህንንም መነሻ በማድረግ በክልሉ በርካታ ታጣቂዎች የኃይል አማራጭን በመተው እና የሰላም ጥሪውን በመቀበል ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ተመልሰዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት 418 ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መከተላቸውን የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አዱኛ አዳሙ ለአሚኮ ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ መደበኛ ሕይወታቸውን መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።
አሁን ላይም በተለያዩ ዘርፎች በመሠማራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው ያስረዱት።
ኅብረተሰቡ በየጊዜው የሰላም ሁኔታው እንዲረጋጋ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት።
መንግሥት አሁንም የሰላም በሩ ክፍት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ይህን የማይቀበሉ ታጣቂዎች ላይ የሕግ ማስከበር ሥራው በተጠናከረ መንገድ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
