ከቃላት የዘለለ የተግባር ክንድ በአረንጓዴ አሻራ

10
🌱
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በደን መመንጠር እና በአየር ንብረት መዛባት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይሁን እንጂ በ2011ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ ለመቀየር የተነሳ ትልቅ ብሔራዊ ንቅናቄ እንደኾነ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሪፖርቶች ላይ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ይህ ሥራ ተራ የዛፍ ተከላ ፕሮጀክት አይደለም። የትውልድ ሕልውናን የማስቀጠል ዘመቻ እንጂ። አረጋውያን፣ እናቶች፣ ወጣቶች እና ሕጻናት በኅብረት ወጥተው መሬት ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ሲቆፍሩ እና ችግኝ ሲተክሉ ማየት የተለመደ ትዕይንት ኾኗል።
በአንድ ጀምበር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ዓለምን ያስገረመው የኢትዮጵያውያን ክንድ በተፈጥሮ ላይ የተደቀነውን አደጋ በጋራ መመከት እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል።
የአረንጓዴ አሻራ ትልቁ ስኬት ችግኝ መትከሉ ላይ ብቻ አይደለም። የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ እና በማጽደቅ ረገድ የተመዘገበው ስኬትም ትልቅ ነው።
ዛሬ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎች መሬት ይዘው ማደግ ጀምረዋል። ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ ፍሬ እያፈራ ይገኛል። ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፍራፍሬ (አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ የቡና ) ችግኞች ተተክለዋል። እነዚህም ለአርሶ አደሮች ተጨማሪ ገቢ እና የምግብ ዋስትናን እያረጋገጡ ነው።
ደርቀው የነበሩ በርካታ ምንጮች እና ወንዞች የአፈር መሸርሸር በመቀነሱ እና መሬቱ ውኃ የመያዝ አቅሙ በመጨመሩ ምክንያት ዳግም መፍለቅ ጀምረዋል። በዋና ዋና ከተሞች የተገነቡት የአረንጓዴ ሥፍራዎች እና መናፈሻዎች የከተማዎችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ማረፊያ እና ንጹሕ አየር መተንፈሻም ኾነዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) እና የዓለም አቀፍ የደን ምርምር ማዕከል (CIFOR) መረጃ እንሚያሳየውም የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮጵያውያን ትምህርት የሰጠ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ እና ለዓለም ጭምር ትልቅ ትምህርት የሰጠ ተግባር እንደኾነ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ከሚደረጉ ንግግሮች ይልቅ መሬት ላይ የሚወርዱ ተግባራዊ ሥራዎች ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጡም አሳይቷል።
ዛሬ የምንተክላት አንዲት ችግኝ ነገ ለልጆቻችን የምታስጠልል ታላቅ ዛፍ ትኾናለች። ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራዋ አማካኝነት ለምድር የምታበረክተው አስተዋጽኦ ነገ ሀገሪቱን በወርቅ ቀለም የሚያስመሰግናት የታሪክ አሻራ ኾኖ ይቀጥላል።
እያንዳንዱ የቆፈርነው የችግን መትከያ ጉድጓድ፣ የተከልነው ችግኝ እና ያፈሰስነው የውኃ ጠብታ የነገዋን ለምለም እና ውብ ኢትዮጵያ የመገንቢያ ጡቦች ናቸው። አሻራችን አረንጓዴ ነው፤ ተስፋችንም እንዲሁ፤ “ከቃላት የዘለለ የተግባር ክንድ በአረንጓዴ አሻራ” አርፏል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዲፕፌክ (Deepfake) ምንድን ነው?
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን 418 ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።