🇪🇹የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎች የማንም ሳይኾኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጾች ናቸው።

2

 

በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ዛሬ ካለችበት ሁኔታ ወደተሻለ ነገ ለመሻገር የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ታላቅ ተስፋን ሰንቋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ኮሚሽኑ ሁሉንም ያካተተ የአጀንዳ የማሠባሠብ ሂደት ለመከተል በርካታ ርቀቶችን ተጉዟል። በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች የሕዝብ ተወካዮችን፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማትን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ የውይይት እና የአጀንዳ ማሠባሠብ መድረኮችን አካሂዷል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ 👩‍💼ሴቶች እና ወጣቶች፣⛪🕌 የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ♿አካል ጉዳተኞች፣ 👩‍🏫መምህራን እና 👥የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች በቀጥታ እንዲሳተፉ ተደርጓል። ይህ ስብጥር አጀንዳዎቹ የጥቂት ልሂቃን ብቻ ሳይኾኑ የጠቅላላው ማኅበረሰብ ድምጽ እንዲኾኑ አድርጓል።

ኮሚሽኑ በአካል መገኘት ለማይችሉ (በተለያዩ ምክንያቶች ድምጻቸው ለማይሰማ) የኅብረተሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ሀሳቦችን በጽሑፍ፣ በዲጂታል አማራጮች (በድረ-ገጽና በልዩ መተግበሪያዎች) እንዲሁም በፖስታ ሳጥን ቁጥሮች አማካኝነት እንዲልኩ ምቹ ሁኔታዎችንም ፈጥሮ ነው አጀንዳ ያሰባሰበው።

ኑሯቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) ማኅበረሰብ ድምጽ ለማካተትም በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነመረብ እና በአካል በመገኘት ውይይቶች ተደርገዋል።

በሀገሪቱ ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ አለመተማመን ለመቅረፍ ኮሚሽኑ ሁሉንም የፖለቲካ ኀይሎች ለማነጋገር ሰፊ የውይይት ሥራዎችንም ሠርቷል።

የተሠበሠቡ አጀንዳዎችንም ወደ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች አደራጅቶ ለምክክር ይፋ አድርጓል።🔗 ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸው እነዚህ ዋና ዋና አጀንዳዎች ተራ የንድፈ ሀሳብ ሰነዶች አይደሉም። ከሀገሪቱ ሁሉም ማዕዘናት ሁሉ የበቀሉ የዕውነተኛ ሕዝባዊ ድምጾች ነጸብራቅ ናቸው እንጂ።

📌እነዚህ አጀንዳዎች ከላይ ወደ ታች በመንግሥት ወይም በፖለቲከኞች የተጫኑም አይደሉም። ከቀበሌ ጀምሮ እያንዳንዱን ዜጋ ባሳተፈ መልኩ የተቃኙ ዕውነተኛ የኢትዮጵያውያን ሀሳቦች ናቸው። ስምንቱ አጀንዳዎች የማንኛውንም ልዩ ቡድን፣ ወገን ወይም የፖለቲካ ኀይል ፍላጎት ብቻ የሚያንጸባርቁም አይደሉም። ይልቁንም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ህልውና፣ ሰላም እና የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ያለውን ስጋት፣ ጭንቀት እና ተስፋ ያቀፉ የሁሉም የጋራ ሀብቶች ናቸው።

ሂደቱ በምንም ዓይነት የውጭም ኾነ የውስጥ አካል አድሏዊ ጣልቃ ገብነት ሳይበከል በኢትዮጵያውያን ሉዓላዊ ፈቃድ እና ባለቤትነት ብቻ የሚመራም ነው። አሁን ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች፣ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ከሁሉም የኑሮ ደረጃዎች የተወከሉ 4ሺህ ኢትዮጵያውያን በአንድ ታላቅ መድረክ ዙሪያ ተሠባሥበው እየመከሩ ነው። በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተወካዮቹ ያለምንም ፍርሃት እና ተጽዕኖ በነጻነት በመወያየት የሀሳብ የበላይነትን ያሰፍናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በልዩነቶች ውስጥ ያሉትን የጋራ እሴቶች በማጉላት፣ ለዘመናት የዘለቁ ቅሬታዎችን በውይይት ፈትተው የጋራ ስምምነት ላይ ይደርሳሉም ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

🌟በጥቅሉ ይህ ታሪካዊ ምክክር የትላንት ቁስሎችን አክሞ፣ የዛሬን ልዩነቶች አቻችሎ፣ የነገዋን ጠንካራ እና አስተማማኝ ኢትዮጵያን ለመገንባት የተዘረጋ ታላቅ ድልድይ ነው። መላው ኢትዮጵያዊ በጋራ አጀንዳዎቹ ላይ መክሮ በአንድነት የሚቆምበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚጻፍበትም ነው። ልዩነቶችንም በውይይት መፍታት እንደሚቻል በተግባር ይታያል።ለትውልድ የሚተርፍ፣ ፍትሕ እና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በአንድ ድምጽ ለሀገር መቆምም ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ይጠበቃሉ።

#ኢትዮጵያ #ሀገራዊ_ምክክር #የጋራ_አጀንዳ_ሰላም_እና_አንድነት

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

✍️ በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🔥 የኢትዮጵያን መፍረስ የሚመኙ ታሪካዊ ጠላቶችን ምኞት ያመከነው ታላቁ ጉባኤ!