
ፍኖተሰላም: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመኖ አቅርቦት
የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን ለማሳደግ እና ዘርፉ የሚገባውን ጥቅም እንዲሰጥ ወሳኝነት አለው።
በእንስሳት ሀብት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እና ኢንተርፕራይዞች ላይ በየጊዜው የመኖ ዋጋ መጨመር በዘርፉ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድርም ይስተዋላል።
የቡሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ይህንን ችግር የሚፈታ እና በቀላል ወጭ መኖ ማዘጋጀት የሚችል በኤሌክትሪክ የሚሠራ ማሽን ሠርቷል።
ማሽኑ የጥራጥሬ እና የዕጽዋት ግብዓቶችን በመጠቀም የተመጣጠነ መኖ ማዘጋጀት የሚችል መኾኑን በኮሌጁ የእንስሳት እርባታ አሠልጣኝ መምህር እና የፈጠራ ሥራው አባል ሰማኸኝ ጥሩሰው ተናግረዋል።
በተለይ በዘርፉ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦችም ይሁን ባለሀብቶች ለእንስሳት መኖ ከፍተኛ ገንዘብ ወጭ ስለሚጠይቅ ይህን ችግር ለመፍታት የፈጠራ ሥራው እንዳነሳሳቸው ነው መምህሩ የገለጹት።
የሠሩት ማሽን እስከ 350 ሺህ ብር ወጭ ብቻ በማውጣት የተመጣጠነ መኖ ማዘጋጀት የሚያስችል መኾኑን አስረድተዋል።
ይህም በዶሮ እርባታ፣ በማድለብ እና በወተት ላም እርባታ ለተሰማሩ ሁሉ ችግራቸውን የሚያቀል ነው ብለዋል።
በማሽኑ የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ በማዘጋጀት ከዚህ በፊት ከፋብሪካዎች ሲገዙት ከነበረው ከአንድ ኩንታል እስከ 1ሺህ ብር ወጭ ማስቀረት የሚችል ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
የቡሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አምሐ ዘውዱ ኮሌጁ ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲኾኑ የተለያዩ ተግባራትን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኮሌጁ የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ተግባር በመቀየር እና በብዛት በማምረት ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተደራሽ በማድረግ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
#አሚኮ_ዜና #የፈጠራ_ሥራ #የቡሬ_ቴክኒክ_ኮሌጅ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ ፦ ንጉሥ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
