
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ከሚዲያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትሯ እናትዓለም መለሰ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም፣ በንቃት እና በኃላፊነት በምርጫ ሂደቱ በመሳተፍ ለዴሞክራሲ ያለውን ጽኑ እምነትና የማይናወጥ ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል ብለዋል። ሚድያው ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ሕዝቡ ድምፁን በነፃነት በመስጠት የሀገሩ ዕጣ ፈንታ በዜጎች ፈቃድ እንደሚወሰን አሳይቷል፤ ይህም የአንድ አካል ሳይሆን የመላው ሕዝብ ድል፣ የዴሞክራሲ ድል እና የኢትዮጵያ ድል መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ታሪካዊ ሂደት የኢትዮጵያ ልጆች የሆኑ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች የማይረሳ ሚና ተጫውተዋል ያሉት ሚኒስትሯ የእውነተኛ ታሪክ ነጋሪዎች የመረጃ ምንጭ ሆነው ሕዝብን በማሳወቅ፣ ለተሳትፎ በማንቃት፣ ሀሰተኛ መረጃዎችንና አፍራሽ ትርከቶችን በድፍረት ተጋፍጠው በማጋለጥ ትልቅ ገድል ሠርተዋል ነው ያሉት።
የተዛቡ ትርከቶችን በእውነት በመመከት እና የሀገሪቱን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም በማሳየት የዴሞክራሲ ጉዞው በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ሚድያዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውም ተገልጿል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለመረጠው ሕዝቧ፣ ለዴሞክራሲ ቁርጠኝነቱን ላረጋገጠው ዜጋ፣ እውነትን ለተናገሩት ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ከልብ ታመሰግናለች ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሕዝቡ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ታሪክ አዲስ ገጽ ጽፏል፤ ጋዜጠኞቹ ደግሞ ያንን ታሪክ በእውነት መዝግበው ለትውልድ አስቀምጠዋል ሲሉ ገልፀዋል።
#አሚኮ_ኢትዮጵያ #ሚዲያ #ምርጫ #ምስጋና
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
