ኤርቪን ማሲንጋ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ምልከታ እና የሁለትዮሽ ትብብሩን የማጠናከር ቁርጠኝነት

9
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የሚመራ የልዑካን ቡድን በጎንደር ከተማ ቆይታው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየሠራቸው ያሉ የመማር ማስተማር እና የሕክምና ሥራዎችን ተመልክቷል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎችም ለልዑክ ቡድኑ አቀባበል አድርገዋል።
ልዑኩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በዩኒቨርሲቲው አጼ ቴዎድሮስ ግቢ በሚገኘው የሀሪ ኤስ ትሩማን አሜሪካን ኮርነር (የቤተ-መጻሕፍት) ማዕከል ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።
​በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ የሕክምና ሆስፒታል ቆይታቸው የሆስፒታሉን የቲቪ፣ ኤች አይ ቢ እና ሎሎች የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን ተመልክተዋል።
የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎች በአሜሪካ መንግሥት እየተደገፈ የቲቢ በሽታ ለመከላከል ታልሞ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን የህክምና አገልግሎት የሥራ ሂደት በተመለከተ ገለጻ ተሰጥቷቸዋል።
ማዕከላቱ በግብዓት እንዲጠናከሩ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ባዩት ነገር ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
አምሳደሩ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትምህርት፣ በምርምር፣ በጤና አገልግሎት እና በተቋማዊ አጋርነት ዘርፎች ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩም አሳውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ራዕዩን ለማሳካት የሚያደርገው ሂደት ውጤታማ እንዲኾን አሜሪካ ከሚገኙ አቻ ተቋማት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በፈረንጆቹ በታኅሣሥ 2025 ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈራረመው የ1 ነጥብ 466 ቢሊዮን ዶላር የሁለትዮሽ የጤና ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማጠናከር እየደገፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ውስጥ ከሚሠሩ የሰብዓዊነት አሥፈጻሚዎች ጋር ተገናኝተው አሜሪካ ክልላዊ የመቋቋም አቅምን በማጎልበት ፈጣን፣ የበለጠ ተጠያቂነት ያለው እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የምላሽ ሞዴል ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የአሜሪካ መንግሥት የክፍለ ዘመን የሳይንስ፣ የጤና እና የማኅበረሰብ እድገት አጋርነት ያለው መኾኑን ገልጸዋል።
የልዑኩ ጉብኝት ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ ለሚገኘው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት የተሻለ እንዲኾን የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
የአምሳደሩ ጉብኝት ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር ለሚያደርገው ጉዞ ስኬታማነት ድርሻው የጎላ መኾኑንም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በተሠራው ሥራ በርካታ የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ተደርጓል።