የፍትሕ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን – ከዲጂታል ዳኝነት እስከ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ስኬት

3
⚖️
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶችን የ2018 በጀት ዓመት እና የሦሥት ዓመታትን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
ክልል ፍርድ ቤቶችን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን ማኅበረሰብ እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ስለመኾኑ በመድረኩ ተመላክቷል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ባዬ ጌታቸው እንደገለጹት በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁሉ አቀፍ የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል። የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱንም ጠቁመዋል።
የዳኝነት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የተከናወኑት ተግባራት ለባለጉዳዮች ትልቅ እፎይታን የሰጡ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል።
📲በኢ-ፋይሊንግ ሥርዓት አማካኝነት መዝገቦች ስማርት በኾነ መንገድ እየተመዘገቡ ባለጉዳዮች በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው እስከ ሰበር ያሉ ክርክሮችን መከታተል የሚያስችል ሥርዓት መተግበሩንም ነው የጠቆሙት።
📊 በዚህም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ የተገልጋዮች እርካታ ወደ 77 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል። በከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ ከቀረቡ መዝገቦች 85 በመቶ የሚኾኑት ውሳኔ የተሰጠባቸው ናቸውም ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ትዕግስት ዳኛቸው እንደገለጹት የሦሥት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን መሠረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ ሥራዎች ማከናወናቸውን አንስተዋል።
🏡በ255 ቀበሌዎች ላይ ተቋቁመው የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ጉዳዮች ያለ ተጨማሪ ወጭ መፍታት ስለመቻሉም አንስተዋል።
የማኅበረሰቡ የፍትሕ አገልግሎት እርካታ ከ71 በመቶ በላይ ስለመድረሱም ጠቁመዋል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ ሕንጻ ግንባታ በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትራቴጅክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፍሬው ታደሰ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የተሻለ ውጤት መጥቷል። በክልሉ ከቀረቡ መዛግብት ውስጥ ከ94 በመቶ በላይ የሚኾኑት እልባት አግኝተዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በአራቱም ምድብ ችሎቶች፣ በ14ቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና በ27ቱ የፓይለት ወረዳ ፍርድ ቤቶች ዲጂታል የዳኝነት አገልግሎት መሥጠት መቻሉንም ገልጸዋል።🖥️
በአጭር ጊዜ ከ1ሺህ 200 በላይ ቀበሌዎች ላይ የባሕል ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም አብራርተዋል።
🚀በቀጣይም በሁሉም ቀበሌዎች የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ባለጉዳዮች ወጭ ሳያወጡ፣ ርቀው ሳይጓዙ፣ በየአካባቢያቸው ችግሮቻቸው እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ቀጣዩ ጊዜ ጠንካራ የጤና ሥርዓት የምንገነባበት ይኾናል” ዶክተር መቅደስ ዳባ
Next articleዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በተሠራው ሥራ በርካታ የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ተደርጓል።