
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እያከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በየዘመኑ የሚከሰቱ በሽታዎችን በመቋቋሞ ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተቋም መገንባት ችለናል ነው ያሉት።
እያንዳንዱ የተቋሙ ባለሙያ በመቶ ዓመት ጉዞ ውስጥ የከፍለው ዋጋ ሕዝባዊ አመኔታን እንዲያገኝ አስችሎታልም ብለዋል።
መንግሥት የጤናውን ዘርፍ በመደገፍ ተደራሽ እንዲኾን ይሠራል ነው ያሉት። የጤና ተቋማት አሠራር ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለው እና በመረጃ የተመሠረተ እንዲኾን የጤና ፖሊሲን ለመተግበር ዝግጁ እንደኾኑም ጠቁመዋል።
ቀጣይ ጉዞዎች በፍጥነት የሚሄዱበት እና የሕዝብ መረጃ በትክክል የሚያዝበት ሊኾን እንደሚገባም አብራርተዋል። በቀጣይ ጠንካራ የጤና ሥርዓት የሚገነባበት እንደኾነም አረጋግጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሳይንስ እና በሕዝብ ጤና ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት የሚያከብር ታሪካዊ ክስተት መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት መሥራች አባል እንደኾነች በማስታወስም ኢንስቲትዩቱ በሕዝብ ጤና፣ በምርምር እና በላቦራቶሪ አገልግሎት በአፍሪካ ከቀዳሚ ተቋማት መካከል መኾኑን አድንቀዋል።
በተጨማሪም እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እና ድንበር ተሻጋሪ የጤና ችግሮች ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የዓለም ጤና ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት ለመሩ ለቀድሞ መሪዎች እውቅና እና ምሥጋና ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጸቀ ሥላሴ ተሰጧቸዋል።
#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ: አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
