በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ነው።

4
የአማራ ክልል ከተማ ልማት ክላስተር የክረምት ሥራዎች የመስክ ሱፐርቪዥን የውይይት መድረክ አካሂዷል። የክላስተር ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ መሐመድ ጀማል (ዶ.ር) በአሁኑ ወቅት የ90 ቀናት የክረምት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውቀዋል። ክረምቱ የዝግጅት ብቻ ሳይኾን የመደበኛ ሥራ ምዕራፍ በማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በክረምቱ ከሚሠሩ በርካታ ሥራዎች መካከል መጠናቀቅ ያለባቸውን የኮሪደር ልማት ሥራዎች በፍጥነት አጠናቅቆ ለነዋሪው ክፍት ማድረግ፤ ስማርት ከተማን ጨምሮ ከተሞችን ጽዱ እና ማራኪ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና እና የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚያስችሉ ስልቶች ተነድፈው በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። በከተሞች እየተገነቡ ያሉትን የገበያ የመሸጫ ማዕከላትን በማረጋገጥ ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
በየዞኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት የልየታ ሥራ ተከናውኖ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። በከተሞች ጾም የሚያድር መሬት አይኖርም በሚል መሪ ቃልም የከተማ ግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የኪራይ ሰብሳቢነት እና የሙስና ችግሮችን ለመፍታት የትግል ሰነድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። በአራት ማዕከላት የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሁሉም ዞኖች ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ስለመኖሩም አንስተዋል።
ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ ሥራዎች በትኩረት ይሠራሉ ነው ያሉት። በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና ኮንትሮባንድ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋልም ብለዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት ከተግባራቱ የሚጠበቅ ዋነኛ ግብ እንደኾነም አስታውቀዋል። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የምርት አቅምን ማሳደግ፤ ሕዝቡን ያሳተፈ የልማት ንቅናቄ በመፍጠር ማኅበረሰቡን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በመድረኩ ከተገኙ የተቋማት መሪዎች መካከል የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዮሐንስ አማረ በክረምቱ ከ615 በላይ የሀገር ውስጥ አልሚዎችን ለመሳብ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በዓመቱም ከ30 በላይ አዳዲስ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ለመሳብ መታቀዱን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት መሬት ወስደው ወደ ሥራ ባልገቡ ከ270 በላይ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።
ይህ የቁጥጥር ሥራ በክረምቱ ወቅት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ውሳኔ ላገኙ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሬት ምላሽ ለመስጠት ዕቅድ እንደተያዘም አንስተዋል።
የክልሉ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ እስከ መስከረም መጨረሻ ሰባት ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዷል ብለዋል። የድንኳን እና የእሁድ ገበያዎችን በማስፋት የገበያ ተደራሽነትን ማስፋት ትኩረት ይሰጠዋል ነው ያሉት።
በክረምቱ ከ150 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊዋ ምሳዬ መኮነን ናቸው።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ግንባታዎች ለሀገር ዕድገት የላቀ ድርሻ አላቸው” አቶ አለምዓንተ አግደው
Next article“ቀጣዩ ጊዜ ጠንካራ የጤና ሥርዓት የምንገነባበት ይኾናል” ዶክተር መቅደስ ዳባ