ሕጻናትን አሳታፊ እና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

4

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በየዓመቱ ሰኔ 9 ቀን የሚከበረውን የአፍሪካ የሕጻናት ቀን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የዘንድሮው የአፍሪካ የሕጻናት ቀን “የተጠበቁ ሕጻናት ለበለጸገ ትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት በኢትዮጵያ ለ35ኛጊዜ እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ እየተከበረ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ቀኑ የሚከበርበት መሠረታዊ ምክንያትም በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት የትምህርት ጥራት እና ፍትሐዊነት ይኑር፤ በቋንቋችን እንማር በሚል እ.ኤ.አ በ1976 ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥቁር ሕጻናት ውሰጥ በመቶዎች የሚቆጠሩት ለሞት በመዳረጋቸው መኾኑን አመላክተዋል።

ይህንን ቀን በማሰብም የአፍሪካ ኅብረት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን ከ1991 ጀምሮ ሰኔ 9ቀን የአፍሪካ ሕጻናት ቀን ኾኖ እንዲከበር ወስኗል ነው ያሉት።

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕጻናት ቀን ሲከበርም ከበዓሉ መከበር ባለፈ እንደ ክልል ለየት ባለ ኹኔታ ሕጻናትን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች በመሥራት እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሕጻናትን ደኅንነት እና መብት የሚያስጠብቁ ሥራዎች በየደረጃው እየተሠሩ ነውም ብለዋል። በተለይም በችግር ውስጥ ያሉ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ሳይነጠሉ ከጊዜያዊ እስከ ቋሚ ድጋፍ እና እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በቀጣይ ለሕጻናት ጥበቃ እና ከለላ በማድረግ ሕጻናት በመብቶቻቸው እንዲጠቀሙ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

#አሚኮ_ዜና #የአፍሪካ_የሕጻናት_ቀን #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🕊የሰላም ተስፋው በዓለም የኢኮኖሚ መረጋጋት እና በነዳጅ ዋጋ ላይ በጎ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
Next articleምርታማነትን የማሳደግ ተስፋ የተጣለበት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ፋብሪካ በማምረት ላይ ነው።