🕊በሰሜን ጎጃም ዞን ከ500 በላይ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።

2

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ኀይሎች ከትጥቅ ትግል በመውጣት የሰላምን አማራጭ በመቀበል ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት እያሳዩ ይገኛሉ። በሰሜን ጎጃም ዞን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም የሰላምን አማራጭ እየተከተሉ ነው።

የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረሥላሴ ታዘብ በዞኑ እየተጠናቀቀ በሚገኘው የ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከ530 በላይ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ገልጸዋል።

ከሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ዕለት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም በኋላ 21 ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን አንስተዋል። የታጣቂ ኀይሉ ከፍተኛ አዛዦች ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት ከተከታዮቻቸው ጋር የሰላምን መንገድ በመከተል እየገቡ መኾኑንም ገልጸዋል።

የዞኑ ማኅበረሰብ ለሰላም ቁርጠኛ በመኾን ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነውም ብለዋል።

ማኅበረሰቡ የሰላም አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን በመንከባከብ፣ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ በማገዝ፣ የሰላም አማራጭን ሲቀበሉ አቀባበል በማድረግ ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳዩ ነው ብለዋል።

የዞኑ የሰላም እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መምጣቱን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው የመንገድ ላይ ዝርፊያዎች እና እገታዎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ እየተሻሻለ የመጣውን የሰላም ኹኔታ ይበልጥ ለማጽናት ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ፣ የጸጥታ ኀይሉ እንዲጠናከር፣ ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲኾን በማስቻል በኩል በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ሰላምን ለማጽናት የጸጥታ መዋቅሩ በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

#አሚኮ_ዜና #ሰላምና_ጸጥታ #ሰሜን_ጎጃም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕፃናት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ኾነው እንዲወጡ እየተሠራ ነው።
Next article🕊የሰላም ተስፋው በዓለም የኢኮኖሚ መረጋጋት እና በነዳጅ ዋጋ ላይ በጎ ተጽዕኖ ፈጥሯል።