
አዲስ አበባ: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ መልዕክት በአፍሪካ ለ36ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ የአፍሪካ ሕጻናት ቀን ይከበራል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ቀኑን ምክንያት በማድረግ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የሕጻናትን መብት እና ደኅነትን ለማስክበር ኢትዮጵያ የፈረመችውን ዓለማቀፍ ስምምነት ለማክበር እና ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያለመ መኾኑን አንስቷል።
የቢሮው ኀላፊ ቆንጂት ደበላ እንደገለጹት በየዓመቱ የሚከበረው የሕጻናት ቀን ሕጻናትን ከጉልበት ብዝበዛ እና ከጾታዊ ጥቃት ለመከላከል እንዲቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
ቢሮው በተያዘው ዓመት ከ3 ሺህ በላይ ሕጻናትን ከጎዳና በማንሳት ከቤተሰብ ጋር ማገናኘቱን ገልጸዋል።
ሴት ታዳጊ ሕጻናት የግል ንጽህናቸውን መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሟላ የሲቪል ተቋማትን በማስተባበር ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ለሕጻናት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ ለ341ሺህ ሕጻናት እንክብካቤ፣ ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የአልሚ ምግብ አቅርቦት፣ ከ1ሺህ በላይ የሕጻናት ማቆያዎች እና የሕጻናትን ቤተሰብ አቅም ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን የቢሮ ኀላፊዋ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሕጻናት ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይትም እየተካሄደ ነው።
#አሚኮ_ዜና #የሕጻናትን _መብት _መጠበቅ #አዲስ_አበባ_ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አየለ ለመስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
