
አዲስ አበባ: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ባለሥልጣኑ ከሃምሳ አንድ በላይ ለኾኑ የሃይማኖት የመገናኛ ብዙኀን ፈቃድ መስጠቱን አስታውቀዋል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኀኑ በሕጉ መሠረት እየሠሩ መኾናቸውን የማረጋገጥ፣ የማረም እና የባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሕዝቦችን አብሮነትን የማጠናከር እና በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚሠራው ሥራ እጅግ የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየታየ ያለውን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ከመግታት አንፃር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በቅርበት መሥራት ውጤታችንን የሚያሳድግ በመኾኑ ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት ጥላቻን እና መከፋፈልን ሲሰብኩ ሲመለከት በ9192 የስልክ መስመር መጠቆም እና ተቋሙም “ኤማአፕ”በተሰኘ የዲጂታል ቁጥጥር ሥርዓት ክትትሎችን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የመግባቢያ ስምምነቱ በሰላም ግንባታ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ከመገንባት አንፃር፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በዜጎች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ያጠናክራል ነው ያሉት።
“ጠንካራ ትብብር ለሀገር ክብር” የተሰኘው ይህ የመግባቢያ ስምምነት ሀገር አቀፍ ሥራዎችን ለሕዝብ ተደራሽ እንዲኾኑ የመገናኛ ብዙኀንን በስፋት ለመጠቀም እና የአቅም ግንባታ ሥራ ለማካሄድ እንደሚያግዝ አንስተዋል።
በተጨማሪም የሀገርን ሰላም ይበልጥ ለማጽናት፣ የዜጎችን መልካም ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት እና ሕዝብን የሚከፋፍሉ እና ወደ ግጭት እንዲገቡ ታሳቢ ተደርጎ የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎችን ለመከላከል የጎላ ሚና አለውም ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #የሐሰተኛ _መረጃን_መከላከል #አዲስ_አበባ_ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
