🚜 ለሜካናይዜሽን እርሻ ትኩረት መስጠቱን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

6

 

​ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሜካናይዜሽን ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሚናው ከፍተኛ ነው።

በአማራ ክልል የሜካናይዜሽን እርሻ በስፋት ከሚተገበርባቸው አካባቢዎች መካከል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ቀዳሚ ነው። የዘንድሮውን የመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች በስፋት ለመሸፈን እና ከፍተኛ ምርት ለማግኘት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
​
​ያነጋገርናቸው ባለሀብቶች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ እንደ ማሾ፣ ሰሊጥ ፣ጥጥ ፣አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ነግረውናል። ባለሀብቶቹ ማሳቸውን በዘመናዊ ሜካናይዜሽን ለመሸፈን ትራክተሮችን የመጠቀም ልምዳቸው ከፍተኛ እንደኾነም ገልጸውልናል።

በተለይም በዘንድሮው የምርት ዘመን የነዳጅ እጥረት የነበረ ቢኾንም እንኳ መንግሥት ለእርሻ ሥራ የሚውል ነዳጅ በወቅቱ እና በበቂ መጠን ማቅረቡ ለሥራቸው ትልቅ ድጋፍ መኾኑንም ተናግረዋል። ይህ የመንግሥት ድጋፍ ማሳቸውን በወቅቱ በሰብል ለመሸፈን እና ውጤታማ ለመኾን ወሳኝ መኾኑን ነው የተናገሩት።
​
​የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ561 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
​በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

በዞኑ ከ1 ሺህ 200 በላይ ትራክተሮች እና የተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎች መኖራቸው ገልጸዋል። ለዚህ የሜካናይዜሽን ሥራ የሚውል ነዳጅ በወቅቱ ተደራሽ መደረጉም አርሶ አደሮች እና ባለሀብቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።

#አሚኮ-ዜና #ሜካናይዜሽን #ወልቃይት #አማራ #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታት ወጣቶች ፋና ወጊ መኾን ይጠበቅባቸዋል።
Next article“የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በቅርበት እንሠራለን” የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሥልጣን