
ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ወጣቶች በኤች አይ ቪ ስርጭት ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት የኤች አይ ቪ ስርጭትን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት ባልተጠበቀ መንገድ አገርሽቶ ለማኅበረሰቡ ስጋት እየኾነ መምጣቱን አስታውቀዋል። ይህም በመከላከል እና በመቆጣጠር በኩል በማኅበረሰቡ ዘንድ መዘናጋት የሚታይበት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን ማሳደግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። በግንዛቤ ፈጠራ ሥራው ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ ለመድረስ ወጣቶች ዋነኛ ቁልፍ ባለድርሻ ናቸው ብለዋል።
የኤች አይቪ ስርጭትን ለመግታት ወጣቶች ፋና ወጊ በመኾን ትልቁን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አሳስበዋል። የንቅናቄ ሥራዎች በቀጣይነት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
የኤች አይ ቪ ስርጭት ለነገ ትውልድ እዳ እንዳይኾን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
#አሚኮ_ዜና #ኤች_አይ_ቪ #ሥርጭት #መከላከል #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
