🕯”በኤሌክትሪክ ኀይል ችግር ምክንያት ወደ ትናንቱ ዘመን መመለሾ የለብንም” የበየዳ ወረዳ ነዋሪዎች

11

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን በበየዳ ወረዳ እና ጠለምት ወረዳዎች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለመኖሩ ማኅበረሰቡን ወደ ትናንቱ ዘመን መልሶታል።

በዞኑ በሁለቱም ወረዳዎች በርካታ ሕዝብ ቢኖርም የመሠረተ ልማት ትኩረት አለማግኘታቸው በዚህ ዘመን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ማግኘት አልቻሉም።

አቶ አማረ መንግሥቴ በበየዳ ወረዳ የድልይብዛ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በወረዳው የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ባለመኖሩ በማኅበረሰቡ ላይ ጫና ማሳደሩን ለአሚኮ ተናግረዋል።

በከተማው ለ8 ሰዓት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጄኔሬተር በመበላሸቱ የወፍጮ አገልግሎት፣ ዳቦ ቤቶች፣ የሞባይል መጠገኛ ሱቆች እና በኤሌክትሪክ የሚከናወኑ ሥራዎች ለአንድ ዓመት መቋረጣቸውን ተናግረዋል።

🕯”እንደገና የኤሌክትሪክ ኀይል ችግር ወደነበረበት ወደ ትናንቱ ዘመን ተመልሰናል” ያሉት ነዋሪው ፤ ማኅበረሰቡ የምግብ እህሎችን ደባርቅ እያስፈጨ በማስመጣት እየተጠቀመ ነው የምንገኘው ብለዋል።

የበየዳ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሸጋው ብርሃን የወረዳው መቀመጫ በኾነችው ድልይብዛ ከተማ ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

በነዳጅ የሚሠራው ጄኔሬትር መበላሸት፣ መልሶ ከተጠገነ በኋላም የነዳጅ አቅርቦት ችግር ምክንያት በከተማው ለአንድ ዓመት💡 የመብራት አገልግሎት መቋረጡን ገልጸዋል። በማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና አሳድሯል ነው ያሉት።

የመንግሥት እና የግል ተቋማት አገልግሎት መቋረጥ፣ የብየዳ፣ የጣውላ፣ የሞባይል ጥገና እና ሌሎች ሥራዎች መቆማቸውንም አንስተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በዞኑ በበየዳ ወረዳ እና በጠለምት ወረዳ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለመኖሩን ተናግረዋል። በዳባት የሚገኘው ሰብስቴሽን ወደ ሁለቱ ወረዳዎች ኃይልን ተደራሽ ማድረግ እንደማይችልም ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በደባርቅ እና በበየዳ ወረዳ የሰብስቴሽን ዝርጋት ለማከናወን ጥናት መደረጉን ነው የጠቆሙት።

የደባርቅ ሰብስቴሽን ግንባታ ጥናቱ ተጠናቆ የጨረታ ሂደት ላይ መኾኑንም ገልጸዋል። የበየዳ ወረዳ ደግሞ በጥናት ላይ መኾኑን ጠቁመዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ከፌዴራል የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በጊዜያዊ መፍትሔነት በጠለምት ወረዳ ደጃች ሜዳ የሶላር ግንባታ ተጠናቋል፤ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጎንደር ሪጅን ዳይሬክተር አያሌው ወርቅነህ በወረዳው የሰብስቴሽን ግንባታ እስኪከናወን ድረስ በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ የበየዳ ወረዳ ሕዝብን በሶላር ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሶላር ኃይል ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል።

#አሚኮ-ዜና #የመብራት-አገልግሎት #በየዳ #አማራ-ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ የወላይታ ዩኒቨርስቲ ተማሪው በሚል ስለሚዘዋወረው መረጃ እናቱ ምን አሉ?
Next articleየኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታት ወጣቶች ፋና ወጊ መኾን ይጠበቅባቸዋል።