
የኢትዮጵያን የዘመናት የአለመግባባት ቋጠሮ ለመፍታት፤ የታሪክ ተቃርኖዎች እና የፖለቲካ ሽኩቻዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በሂደቱ በርካታ መሠናክሎችን አልፎ ኢትዮጵያውያንን በአንድ መድረክ ለአንድ ዓላማ በታሪካዊ ጉባኤ ላይ አሰባስቧቸዋል። 
ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮች እንዲፈቱ፤ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንዲገነባ፤ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፤ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት እንዲገነባ የሚያስችል ብስራትን ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ ተጥሎበታል።
በሂደቱም ሁሉን አቀፍ፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ የኾኑ አጀንዳዎችን የመለየት፤ የማሰባሰብ እና የመቅረጽ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶችም ተካሂደዋል። በዚህ ሂደት አልፎ ዛሬ ላይ ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ ተሳታፊዎችን በአንድ ጠረጴዛ አሰባስቧል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ምክክሩን አካታች፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
የሕዝብ አካታችነትን ለማረጋገጥ ከታች ወደ ላይ የኾነ ስልትን ተከትሏል ነው ያሉት። በሁሉም ክልሎች፤ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደሮች ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውንም አስገንዝበዋል።
በዚህም በመላ ሀገሪቱ 1 ሺህ 234 ወረዳዎችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን ማሠባሠብ መቻሉንም አንስተዋል። በመጨረሻም ለምክክሩ 8 ሀገራዊ አጀንዳዎች ተለይተዋል ነው ያሉት።
ዋና ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት የተቀረጹት አጀንዳዎችም የሕዝቡን ቅሬታ፣ ስጋት፣ ፍላጎት እና ተስፋ ያካተቱ ናቸው። የአጀንዳ ቀረጻ ሂደቱ የዓለም ዓቀፍ ልምዶችን የጥናት ግኝቶችን እና ሳይንሳዊ ሂደቱን የተከተለ ነበር ብለዋል።
በውጤቱም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል እና መተማመን እንዲፈጠር ለማድረግ ተስፋ የተሰነቀበት ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ እና አስተማማኝ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ስለመኾኑም አስታውቀዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለችን ሀገር ለማስረከብ የተጠነሰሰ ጽኑ መሠረት የሚጣልበት ታሪካዊ ዕድል ነው ሀገራዊ ምክክሩ።
#አሚኮ # ኢትዮጵያ
#ሐምሌ_10_2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
