በዚህ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።

4

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ሀገሪቱ ከ2011 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀሳብ አመንጭነት ያከናዎነችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ መራቆት ችግሮችን መፍታት ዓላማው እንደነበር አንስተዋል።

በዚህ መርሐ ግብር በየዓመቱ በአማካይ 25 ሚሊዮን ሕዝብ በመሳተፍ ሕዝቡ የተግባሩ ባለቤት መኾኑን ለዓለም አሳይቷል ነው ያሉት።

በዚህ ምክንያትም ሀገራዊ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ በ2016 ዓ.ም ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ በማድረስ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ መቻሉን ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ በከፍተኛ ሁኔታ የአፈር መሸርሸር እና የደን መጨፍጨፍን በመከላከል የተፋሰሶች የውኃ መጠን በመጨመር የተስተካከለ ፍሰት እንዲኖራቸው አስችሏል ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተከናወኑ ሥራዎች የውኃ ምጣኔን በመጨመር የበጋ ስንዴ ምርታማነትን 280 ሚሊዮን ኩንታል በማድረስ ሀገሪቱ ለስንዴ ግዥ ታወጣው የነበረውን 1 ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት ተችሏል ነው ያሉት።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መጀመር ምክንያት ኢትዮጵያ 2ኛ የአቮካዶ ላኪ ሀገር መኾን አስችሏታል ያሉት ሚኒስትሩ የቡና ምርታማነትም በማደጉ ከ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ለመትከል ግብ የተቀመጠውን 8 ቢሊዮን ቸግኝ ግብ ለማሳካት በትኩረት፣ በቅንጅት እና በባለቤትነት ስሜት መሥራት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

#አሚኮ_ዜና #አረንጓዴ_አሻራ #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ: ኢብራሂም መሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ወደ ማድረግ ዘመን የሚያሸጋግር ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)