
አዲስ አበባ: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) የ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በቢሾፍቱ ከተማ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህን ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተስፋ የሚተከልበት ነው ብለዋል።
የሀገር ሉዓላዊነት በባዕድ ድንበር በመደፈር ብቻ ሳይኾን የሚጣሰው የራስ ሀብት የኾነው የማይተካው አፈር ድንበር አልፎ ሲሄድ ጭምር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ይህን ክብር ለማስጠበቅ የሚተገበር መኾኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለዓመታት በአፈር መሸርሸር ሀብቷን አጥታለች፣ እኛ የአሁኑ ትውልድ ልክ እንደቀደምቶቹ አባቶቻችን የዓድዋ ድል ዳግም የተፈጥሮ ሀብታችንን በመጠበቅ ትውልድ የሚዘክረው የሉዓላዊነት መከበር ገድል እየፈፀምን ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መልዕክት እንደሚካሄድ አንስተዋል። የነገን ብሩህ ቀን ዛሬ በመፃፍ፣ የተስፋ ስሮች ዘልቀው የብልጽግና ግንድ፣ ቅርንጫፍ እና ፍሬ ተስፋፍቶ ሀብት እንዲኾኑ የሚያመላክት መኾኑንም አንስተዋል።
ተስፋ የአረንጓዴ መቀነት ነው፣ ሀገርን ያለብሳል፣ የተራቆተ እና የገረጣን መሬትም ያለመልማል፣ ተስፋ አረንጓዴ ፀዳል እና መንፈስን የሚያድስ አረንጓዴ ወርቅ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ወደ ማድረግ ዘመን የሚያሸጋግር መኾኑን እና መርሐ ግብሩ አፈርን ከስደት፥ ግድብን ከደለል የሚታደግ ስኬታማ የልማት ዓምድ መኾኑን ገልጸዋል።
ከአስር በላይ አዳዲስ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በኢትዮጵያ በማላመድ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ስኬትም ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ቀዳሚ እና በዓለም ዕውቅና ያስገኘውን ይህን ተግባር ይበልጥ በማጠናከት የበለፀገች፣ የተከበረች ሀገርን ለትውልድ ለማስረከብ በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በቀጣይ ወራት በከፍተኛ ርብርብ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬታማ እንዲኾን ችግኝ መትከልን ከሁሉም ተግባራት ቀዳሚ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዚህ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ዋና ግብ መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለኮፓ-32 65 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ አስቀምጣለች ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #አረንጓዴ_አሻራ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ:- ኢብራሂም መሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
