“የዜጎችን እርካታ ለማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባር ብቁ የኾነ የሰው ኃይል መገንባት ነው” ባንችአምላክ ገብረማሪያም

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እና አሥተዳደር ሪፎርም ዙሪያ ከመገናኛ ብዙኀን እና ሕዝብ ግንኙነት መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኅላፊ ባንችአምላክ ገብረማሪያም የዜጎችን እርካታ ለማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባር ብቁ የኾነ የሰው ኃይል መገንባት ነው ብለዋል። የመንግሥት አገልግሎት በየትኛውም ጊዜ ነጻ፣ ግልጽ እና አካታች እንዲኾን እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

በሪፎርሙ ጠንካራ ሠራተኞችን እና ተቋማትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በዚህ ሂደት ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እና የሕዝብ ግንኘነት አካላት ለኅብረተሰቡ እና ለመንግሥት ሠራተኞች ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ ዓባይ መንግሥቴ
በክልሉ ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ሕዝብ የሚፈልገውን ፈጣን፣ ጥራት ያለው እና ታማኝ አገልግሎት ለማቅረብ እየተሠራ ነው ብለዋል። በሪፎርሙ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማስተካከል ሚዲያዎች እና የሕዝብ ግንኙነት አካላት ትልቅ የማስገንዘብ ኀላፊነትን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ሪፎርሙ ብቁ እና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ መሪ እና ባለሙያ በመፍጠር የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የአሚኮ ጋዜጠኛ ካሰው መንጌ ሚዲያው በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመንን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዲገነባ ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል። የሚወጡ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ እንዲኾኑ መከታተል እና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

​የሪፎርም ሥራዎችን ለሕዝብ በማስረዳት እና በሂደቱ ግልጽነት እንዲፈጠር የማድረግ ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት። ሚዲያው ከአሁን በፊት ሢሠራቸው የነበሩ ሥራዎችንም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

​የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አምሳሉ ጎባው ቢሮው ለሪፎርም ተግባሩ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል። ሕዝቡ በሥራ ሂደቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ይጠበቃልም ነው ያሉት።

የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የሕዝብን እርካታ ማሳደግ የጋራ ግብ አድርጎ መሥራት ይገባልም ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #የመንግሥት_አገልግሎት_ጥራት_ማሻሻል #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሀገራችንን ከዓለም ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከላት ተርታ ለማሰለፍ ያስችላል” የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት