
ደሴ: ሰኔ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ ጠዋት በደሴ እና ኮምቦልቻ መካከል ሐረጎ በተባለ ሥፍራ በደረሰ የመኪና አደጋ የ28 ሰዎች ሕይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሰል።
አሁን ደግሞ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ፖሊስ አስታውቋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ እንደገለጸው በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች 31 ደርሷል።
አደጋው የደረሰው በተለምዶ ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ በሚወስደው ሐረጎ “S” መንገድ መታጠፊያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከንጋቱ 12:00 መኾኑን የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ሙህዬ ተናግረዋል።
ተሽከርካሪው ከ100 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ገደል ውስጥ በመግባቱ ሹፌሩን ጨምሮ የ31 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ33 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንም ኮማንደር ጌታቸው ለአሚኮ ገልጸዋል።
ተሽከርካሪው 64 ሰዎችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ እንደነበር ያነሱት ኮማንደር ጌታቸው ተጎጅዎች በደሴ እና በኮምቦልቻ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተደረገላቸው እንደኾነም አንስተዋል።
የአደጋው መንስኤም እየተጣራ መኾኑን አስታውቀዋል።
አሚኮ በአደጋው ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል። ለተጎጅ ቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል።
ዘጋቢ:- ሳሙኤል ኪሮስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
