
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ከእዙ ከፍተኛ መሪዎች፤ የኮር እና ክፍለ ጦር የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ እዙ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ሀገራዊ እና ተቋማዊ ተልዕኮዎችን በስኬት እና በጀግንነት እየፈጸመ መኾኑን ተነስቷል።
የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለመቀራመት የከፈቱባትን ጦርነት ያሸነፈች እና በቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት። ኢትዮጵያውያን ቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ ብለው ወረራዎችን ለመቀልበስ ያደረጓቸው ተጋድሎዎች የሀገር እና የአፍሪካውያን ኩራት ምንጭ ኾነዋል።
ከዚህ ያልተማሩ አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን በቀጥታ ከመውጋት ይልቅ ባንዳዎችን እየቀጠሩ፣ እያሠለጠኑ፣ እያስታጠቁ እያዘመቱ የልማት ደንቃራ ለመኾን ላይ ታች በመሯሯጥ ላይ መኾናቸውም ተመላክቷል።
ይህንን ቀጥተኛ የሀገር ስጋት መንግሥት፣ ሕዝብ እና ሠራዊቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጋራ እየመከቱ ይገኛሉ።
የምሥራቅ እዝ አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ባዕዳን ጠላቶች አሁንም ጥቃታቸውን ቢቀጥሉም ሕልማቸው በጀግናው ሠራዊታችን እንዲመክን እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ባለፈው ግንቦት ወር ብቻ ሀገርን ለማተራመስ እና ምርጫውን ለማደናቀፍ ባደረጓቸው የተቀናጁ ሁለት ጥቃቶች ሽንፈቶችን ተከናንበዋል ነው ያሉት።
የሠራዊቱ መሪዎች ይህንን የባዕዳን ፈረሶች የሚያደርጉትን የጥፋት ግልቢያ በሚገባ ተረድረው እና ብሔራዊ ስጋቶችን በመተንተን የሚመሩትን አሀድ በስጋቱ ልክ በማዘጋጀት የሚመጣውን ማንኛውንም ትንኮሳ እና ውጊያ በድል አድራጊነት መወጣት የሚያስችለውን የወታደራዊ፣ የሞራል እና የሥነ ልቦና ዝግጁነት አሟልተው መገኘት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የባዕዳን እና ባንዳዎችን አፍራሽ ተልዕኮ በማምከን ስለት የያዘውን የጠላት እጅ እየተከታተሉ መቁረጥ የሠራዊታችን የቆየ ልምድ እና ተግባር ነው ብለዋል።
ምሥራቅ እዝ በተሰማራባቸው በሶማሊያ ድንበር አልሸባብን፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ ሸኔን እና ጽንፈኛውን በገቡበት ገብቶ በመደምሰስ የሀገርን ሕልውና እያስጠበቀ መኾኑን ገልጸዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች በእጅ አዙር የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅመው ሀገርን መንግሥት አልባ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ፣ አሁንም ያሉ፣ ወደፊትም ሀገር እንዳታድግ የሚሠሩ በመኾናቸው ሠራዊቱ ይህንን በመገንዘብ በኀላፊነት እና በተጠያቂነት መንፈስ ግዳጁን በድል እንዲፈጽም አሳስበዋል።
መረጃው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
