
የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ የጦርነት እና የትጥቅ ግጭት ማኅደር ኾኖ ቆይቷል። ትውልዶች የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት ሲሞክሩ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይህ የኅይል አካሄድ ሀገሪቱን ለከፋ የሰው ሕይወት መጥፋት እና ለሀብት ውድመት ዳርጓታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ በሰጡበት ወቅት “ተጋጭተን፣ ተዋግተን፣ አንዳችን ሌላችንን ለማስገበር ሞክረን አይተነዋል። ይህ ሁሉ ግን አክስሮናል እንጂ አላተረፈንም፤ አዋርዶናል እንጂ ከፍ አላደረገንም፤ አደህይቶናል እንጂ አላበለጸገንም፤ ከፋፍሎናል እንጂ አልደመረንም። ሀብታችንንም ሊያከማች አልቻለም” በማለት ግጭት እና ጦርነት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ እየጎተቷት መኾናቸውን ተናግረዋል።
ከተማከለች፣ ከበለጸገች እና ሰላም ከሰፈነባት ጠንካራ ሀገር እንጂ ከደከመች፣ ከተበተነች እና ካነሰች ኢትዮጵያ የሚያተርፍ ኢትዮጵያዊ ስለማይኖር ኢትዮጵያን በመነጋገር ሀገርን ወደ ከፍታ ማሻገር እንደሚገባ ተናግረዋል። ያኔ ሥልጣኔያችን፣ ብልጽግናችን እና የዕድገት ደረጃችን ከአኩሪው እና ከረዥሙ ታሪካችን ጋር የተሰናሰለ ይኾናል።
የፖለቲካ ሽኩቻዎችን በጦርነት ለመቋጨት የሞከሩ በርካታ ሀገራት ፈርሰዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውም ተፈናቅለው በየሀገራቱ ተበታትነዋል። የግጭት መዘዝ የሕዝብን ሥነ-ልቦና ይሰብራል፤ የሀገርንም ተቋማዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ከስሩ እንደሚያደቅ እኛም በእኛ ታሪክ አይተናል፤ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
ኢትዮጵያ ዛሬ ከዚህ የጥፋት አዙሪት ለመውጣት ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ደርሳለች። አሁን አስከፊውን የጦርነት ታሪክ በመዝጋት አዲስ የሰላም ምዕራፍን በምክክር እየከፈተች ነው።
የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች እና የሐሳብ ቀለሞች ዛሬ በአንድ አዳራሽ ውስጥ በነጻነት እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ። የተለያየ ድምጽ እና ብሶት ያላቸው ዜጎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የጋራ መፍትሔ እየፈለጉ ነው። ይህ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ባልተገባ ትርክት የተራራቁትን እና የተከፋፈሉትን ኢትዮጵያውያን ወደ አንድነት የሚያመጣ ትልቅ የእርቅ እርምጃ ነው።
ልዩነቶችን በኅይል እና በማግለል ከመፍታት ይልቅ በመደማመጥ መፍታት ዘላቂነት አለው። ጠመንጃ ለጊዜው የኅይል የበላይነትን ያረጋግጥ ይኾናል እንጂ እውነተኛ መግባባት አያመጣም።
ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና የሕዝቦች አብሮነት የውይይት ባሕልን ማዳበር እጅግ ወሳኝ ነው። የሠለጠነ የፖለቲካ ውይይት የዴሞክራሲ ተቋማትን ያጠናክራል፤ የሕግ የበላይነትንም ያረጋግጣል።
በምክክር እና በጋራ መግባባት የምትገነባ ሀገር በቀላሉ በፖለቲካ ማዕበል አትናወጥም፤ ጸንታ ትቆማለች። አሁን የተጀመረው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የነገዋን ጠንካራ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል ዋነኛ መሳሪያ ነው።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በብዕር ኅይል፣ በውይይት እና በጋራ መከባበር መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማሳየት ይገባል ብለዋል።
#አሚኮ #Ethiopia #National_Dialogue
#ባሕር_ዳር ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
