“ቁስሎቻችንን በውይይት አክመን፣ የጸናች ሀገር እንገነባለን!”

6

 

​”እኛ ኢትዮጵያውያን በሕግና ሥርዓት፣ በጀግንነትና በነፃነት አፍሪካን ያበራን የታላቅ ታሪክ ባለቤቶች ነን! በረዥሙ ታሪካችን ውስጥ፣ ልዩነቶችን ከኃይል ይልቅ በተለያዩ የሽምግልና ሥርዓቶች የመፍታት ጥልቅ ልምድ ያለን ሕዝቦች ነን።

​ዛሬ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው! ልጆቿ ከአራቱም አቅጣጫ ተሰባስበው ያልተጠገኑ ቁስሎችን በውይይት ለማከም ታሪካዊ ጉባኤአቸውን ጀምረዋል” ይህ መልእክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ዛሬ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አስመልክቶ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ያስተላለፉት መልዕክት ነው።

በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም በመታደላቸው የተሰማቸውን ታላቅ ኩራትም ገልጸዋል።

​ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፏቸው ዋና ዋና መልዕክቶች፦

📝 አዲስ ታሪክ መጻፊያ “ብዕርና ብራና”፦ ለሚቀጥሉት ሳምንታት አራት ሺህ ተሳታፊዎችን በአንድ ጣሪያ ስር የሚያሰባስበው ይህ ታላቅ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን ታሪካዊ አጋጣሚ የፈጠረ ነው።

🤝 የአዙሪት ስብራት፦ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይለ እርምጃ የሚደመደምበትን የቆየ አዙሪት ሰብረን፣ በንግግርና በውይይት የምንተካበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ለዚህም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል።

🌱 ለውጥና ሰላማዊ ሽግግር፦ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ከሥር ወደ ላይ በዘለቀው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ላይ የተመሰረተው ይህ ጉባኤ፣ በቀላሉ የማይደገምና በዘመናዊ ታሪካችን ውስጥ ግዙፍ ዓላማ ያለው ነው። ፈተናዎቻችንን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን እናጸናለን።

🇪🇹 ለሀገርና ለልጆች ምክክር፦ በዛሬው ዕለት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ መልካም ዘር እንዘራለን። ከየሰፈራችን ወጥተን ለኢትዮጵያ ስንመክር፣ ለልጆቻችን ስንልና እነርሱን እያሰብን ስንወያይ ውጤቱ እጅግ ፍሬያማ ይሆናል።

🛡️ ከውጭ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ፦ በአብሮነት ተስፋን፣ ይቅርታን እና በጋራ መኖርን እንትከል። በሀገር ውስጥ በሚደረግ ውይይትና ይቅርታ ችግሮቻችንን በመፍታት ሀገራችንን ከውጭ ጣልቃ ገብነት እንጠብቅ።

​”ተሳታፊዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ መልካም፣ ለአፍሪካ አስተማሪ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እውነተኛ እረፍትን የሚያመጣ ታሪካዊ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመልእክታቸው።

​📢 እርስዎስ በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር ላይ ምን ዓይነት ተስፋና ምኞት አለዎት? አሳብዎን በኮሜንት ያካፍሉን።
​#ብሔራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ_ትምከር #ዘላቂ_ሰላም #አንድነት #ይቅርታ #Ethiopia

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌍 “የኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋት እና አንድነት ለቀጣናው እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው” አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ