
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል “የነጭ ወርቅ ምድር” በመባል ከሚታወቁ አካባቢዎች መካከል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አንደኛው ነው።
ዞኑ የጥጥ ምርትን በስፋት በማምረት ይታወቃል።
በዞኑ እየተከናወነ ያለው የጥጥ ልማት ለባለሀብቶች ተጠቃሚነት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዞኑ የግብርና ሥራ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ ራሳቸው ሰገድ በ2017/18 የምርት ዘመን በ300 ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ በማልማት ከ2 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ለቀጣዩ የመኸር ወቅትም ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ከ800 ሄክታር በላይ መሬትን በጥጥ ለመሸፈን አቅደው ወደ ማሳ ማጽዳት ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።
ሌላኛው የዞኑ አምራች ባለሀብት አቶ ያዘዘው ሰለሞን በጥጥ ምርት ዘርፍ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተለይም በጥጥ ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ሌሎችም አልሚዎች ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገው ተናግረዋል።
የምርት መጠኑ እና የገበያ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል። ባለፈው የምርት ዘመን በ50 ሄክታር መሬት 750 ኩንታል ጥጥ አምርተዋል። ለዘንድሮው የመኸር ወቅት ደግሞ 250 ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደዋል። አሁን ላይ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኅላፊ አወቀ መብራቱ በዞኑ የጥጥ ምርት አበረታች ውጤት እያሳየ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት 45 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ተሸፍኖ 450 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቷል ነው ያሉት።
ዘንድሮ ደግሞ ይህንን አፈጻጸም ከፍ በማድረግ 80 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ለመሸፈን እና 800 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል። የገበያ ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ፍላጎት ጨምሯል ነው ያሉት። ምርታማነቱ ተስፋ ሰጪ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች የማሳ የማጽዳት እና ለእርሻ የማዘጋጀት ሥራዎችን በስፋት እያከናወኑ መኾናቸውን ነው የጠቆሙት።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
