
ባሕር ዳር: 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን መካከል ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ላይ የሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን የሚያስቆም የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱን የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ አስታውቀዋል።
ስምምነቱ በዕለተ አርብ በስዊዘርላንድ ይፈረማል ተብሏል። የስምምነቱ ዝርዝር ይዘቶች እና ያልተካተቱ ነጥቦች ግን አሁንም እየወጡ ይገኛሉ።
ቢቢሲ እንደዘገበው የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስምምነቱ መጠናቀቁን አረጋግጠዋል። የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ ደግሞ ክስተቱን ለቴህራን የተገኘ ታላቅ ድል አድርጎ አቅርቦታል።
ዩናይትድ ስቴትስ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት የታገደባትን የ12 ቢሊዮን ዶላር የኢራን ሀብት ወይም ንብረት እንደምትለቅ የኢራኑ መኸር (Mehr) የዜና ወኪል በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን የ14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ጠቅሶ ዘግቧል።
ኢራን ማንኛውንም ዓይነት የኑክሌር መሣሪያ የቴክኖሎጂ ልማት እና ምርት ሙሉ በሙሉ እንደምታቆም በትላትናው ዕለት በሰበር መረጃ ሲወጣ ውሏል።
ስምምነቱ መቃረቡን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ “ነዳጅ ይፈሳል” የሚል መፈክር አሰምተዋል። ይህንን ማስታወቂያ ተከትሎም የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጦርነት በዕለተ አርብ በሰላም ስምምነት ፊርማ ይቋጫል መባሉን ተከትሎ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን በኢራን ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ለማንሳት ዝግጁ መኾናቸውን ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
አራቱ ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢራን የኑክሌር መርሐ ግብሯን በተመለከተ ለምትወስዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች ምላሽ ለመስጠት ማዕቀቡን እንደሚያነሱ ገልጸዋል።
ሀገራቱ “ኢራን በፍጹም የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት መኾን የለባትም፤ ይህንን ግብ ለማሳካትም ከአሜሪካ፣ ከኢራን እና ከዓለም አቀፉ የኑክሌር ኃይል ኤጀንሲ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን” ብለዋል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
