
ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1ኛው የኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በባሕር ዳር ከተማ ተከናውኗል።
በዕለቱ የተገኙት የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ መንግሥት ለስፖርት ቱሪዝሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በአብዛኛው ከተሞቻችን የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾኑ ከፍተኛ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በዚህም “ክልሉ በርካታ የስፖርታዊ ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅም እንዳለው” ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየምን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። የዛሬው ሁነት በርካታ ውድድሮችን ማስተናገድ የምንችል መኾኑን፤ ሕዝቡም ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር ያለው እና ድጋፍም የሚሰጥ መኾኑን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
በቀጣይ በባሕር ዳር ከተማ ብቻ ሳይኾን በክልላችን ባሉ ሌሎችም ከተሞች ተመሳሳይ ውድድሮችን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ውድድሩን በብቃት እንደምናዘጋጀው በመተማመን ዕድሉን ለሰጠው ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በውድድር ለተሳተፉ እና ላስተባበሩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
