“ሠራዊቱ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን የፅንፈኞችን አንገት ያስደፋ እና ሕዝብን ያኮራ ተግባር ፈጽሟል” ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ

9

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ እና በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ በመሩት መድረክ፣ ምርጫው ሕዝብ ሰላምን እንደሚፈልግ ያረጋገጠበት ሁነት መሆኑ ተመልክቷል።

በመድረኩ የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ
“ሠራዊቱ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን የፅንፈኞችን አንገት ያስደፋ እና ሕዝብን ያኮራ ተግባር ፈጽሟል” ብለዋል።

ሌተናል ጀነራል መሐመድ እንደተናገሩት፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፅ በመስጠት በቀጣይ 5 ዓመታት ይመሩኛል የሚላቸውን ለመምረጥ ያደረገውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለመበጥበጥ የመጣው ኀይል በአብዛኛው ተደምስሷል።

ሕዝቡ የታሪካዊ ጠላቶችን እና የባንዳዎችን ፉከራ ሳይበግረው በሁሉም ቦታ ወጥቶ ድምፁን በመስጠት በቀጣይ 5 ዓመታት ይመሩኛል ያላቸውን ሕገመንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ በመምረጥ የፅንፈኛውን ማስፈራራት ከምንም ሳይቆጥር ከንቱ አድርጓል ብለዋል።

ሕዝቡ በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን መንግሥት የሚመሠረተው በምርጫ ካርድ ብቻ በመሆኑ ሰላም ፈላጊነቱን ያረጋገጠበት ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

ለነዚህ ድሎች መሳካት በየጊዜው የተደረጉ የሕግ ማስከበር ዘመቻዎች ውጤት መሆናቸውን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

ይህ የሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት እንዲቀጥል ሠራዊቱ ከሀዲ ቡድኖችን እና ጽንፈኞችን የገቡበት ገብቶ በአጭር ጊዜ በመደምሰስ የቀጣናውን ሰላም የማረጋገጥ ዋነኛ ግዳጁን በብቃት እየፈፀመ እንደሚገኝ ሌተናል ጀነራል መሐመድ አስገንዝበዋል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ ፣ ኅብረተሰቡ ፅንፈኛዉ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን እና “እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትፍረስ” ብለዉ ሌት ከቀን የኢትዮጵያን ዕድገት ከሚፃረሩ ኀይሎች ጋር በጋራ መሥራቱን፤ በሰፈርና በጎጥ ተቧድኖ የግል ጥቅሙን እያግበሰበሰ ያለ ዘራፊ ቡድን መሆኑን በመረዳቱ አምርሮ መጥላቱን በምርጫ አረጋግጧል ብለዋል።

ምሥራቅ ዕዝ በአማራ ክልል ሕግ ለማስከበር ከገባ ጀምሮ በርካታ ስምሪቶችን በማድረግ ፅንፈኛዉን በገባበት በመግባት እየተከታተለ በመደምሰስ ሀገር የማፍረስ ዕቅዱን ማክሸፍ በመቻሉ ለዚህ ተግባሩም የክልሉ አመራሮች፣ የዞንና የከተማ አሥተዳደሮች ምስጋና አቅርበዋል ነው ያሉት።

ዕዙ በሰሜንና በምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ እና በደቡብ ጎንደር ቀጣናዎች በመግባት በሀገር ከሀዲ ፅንፈኛዉ ላይ ከፍተኛ ምት በማሳረፉ የአካባቢዉ ማኅበረሰብ ከፀጥታ ስጋት በመዉጣት ወደ ልማቱ እንዲያተኩር በማድረጉም በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ፣ የባሕርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማዉ እና የዞን አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉ የፀጥታ ኀይልም ከሠራዊቱ ጋር ግዳጅ ተሰጥቶት መስዋዕትነት በመክፈል ሰላምን እያረጋገጠ እንደሚገኝና ልማቱ እንዲቀጥል፣ ዜጎች የዕለት ከዕለት ሥራቸዉን እንዲሠሩ ሚናዉን እየተጫወተ መሆኑንም በዉይይቱ የተሳተፉ የክልሉ የፀጥታ ኀይል ተወካዮች ተናግረዋል።

የዉይይት መድረኩ ያለፈውን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በመገምገም በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች አቅጣጫ በማስቀመጥ መጠናቀቁን የዘገበው ምሥራቅ ዕዝ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ውድድሩ የባሕር ዳርን ውበት እና ሰላማዊነት ለዓለም የመሰከረ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next article“ክልሉ በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅም አለው” አቶ መልካሙ ጸጋዬ