“ውድድሩ የባሕር ዳርን ውበት እና ሰላማዊነት ለዓለም የመሰከረ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

13

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በውድድሩ መዝጊያ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ውድድሩ ባሕር ዳር ከተማ የሰላም ከተማ መኾኗን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። ይህ ውድድር በባሕር ዳር እንዲካሄድ የወሰኑ እና በቦታው ተገኝተው ለታደሙ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል።

ባሕር ዳር በታላቁ የጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የምትገኝ እና ታላቁ የዓባይ ወንዝም የሚያልፍባት በመኾኑ ውብ የውኃ ዳር ከተማ ናት ብለዋል። ጽዱ እና አረንጓዴነቷም ለቱሪስቶች የምትመች፣ ለነዋሪዎቿም ምቹ እና አልሚዎችም መርጠዋት ሃብታቸውን የሚያፈስሱባት ከተማ መኾኗን አንስተዋል።

የ1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በባሕር ዳር መካሄዱ የከተማዋን ውበት እና ሰላማዊነት ለዓለም ሕዝብ የነገረ ኹነት ነውም ብለዋል። ከተማዋ የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል እንድትኾን ታልሞ እየተሠራባት ያለች ከተማ ስለመኾኗም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የባሕር ዳር ስታዲየም ሥራ እየተጠናቀቀ ነውም ብለዋል። ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን ማስተናገድ የሚቻልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አሉ፤ አዳዲስም እየተገነቡ ነው ብለዋል። በተለይም በቀጣዩ ዓመት የሚጠናቀቁ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል። ይህም ባሕር ዳርን ሁሉ የተሟላላት ዘመናዊ ከተማ ያደርጋታል ነው ያሉት።

“ባሕር ዳር ከተማ ሰላሟን ጠብቃ እየለማች ያለች ከተማ ናት፤ የባሕር ዳር ወዳጆች ሁሉ ኑ እና ጎብኟት” በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ከልል ከተሞች በለውጥ ላይ ናቸው።
Next article“ሠራዊቱ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን የፅንፈኞችን አንገት ያስደፋ እና ሕዝብን ያኮራ ተግባር ፈጽሟል” ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ