የአማራ ከልል ከተሞች በለውጥ ላይ ናቸው።

9

 

ወልድያ: ሰኔ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ክልላዊ የኮሪደር ልማት ግምገማ እና የልምድ ልውውጥ በወልድያ ከተማ አካሂዷል።

ወልድያ ከተማን ጨምሮ ሰባት ከተሞች የኮሪደር ልማት አተገባበራቸውን ተሞክሮ አካፍለዋል። የወልድያ ከተማ መሪዎች ልማቱን ወደ ሕዝብ አውርደው በማስረፃቸው ለልማት ሥራው ስኬት ምክንያት ነው ብለዋል።

ሰው ላይ መሥራት፣ ከተማን የሚያሻግር ትውልድን መፍጠር ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ተሞክሯቸውን ያካፈሉን ከተሞች እና በተግባር ያየናት ወልድያ ምሳሌዎች ናቸው ብለዋል።

እየተሠራ ያለው ልማት የተጀመረ እንጂ ያልተጨረሰ ሥራ በመኾኑ የከተማ ነዋሪዎችን ፍላጎት የሚያረካ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሥራ መሥራት የቀጣይ የመሪዎች ኀላፊነት እንደኾነ አስረድተዋል።

የጸጥታ ችግር ምክንያት ሊኾን እንደማይችል ከወልድያ ከተማ አረጋግጠናል ያሉት ተሳታፊዎቹ ከልማት ወደኋላ ከማለት ይልቅ ሠርቶ ማሸነፍ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የአማራ ከልል ከተሞች በለውጥ ውስጥ ናቸው ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩን እየተሻገሩ ሥራ ለሠሩ መሪዎች ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የምንሠራቸው ኘሮጀክቶች በበቂ ቅድመ ዝግጅት ሊኾን ይገባል የሉት ኀላፊው ከዚህ መድረክ በኋላ በርካታ ከተሞች ተለውጠው ልናይ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ በወልድያ በተቀናጀ አቅም አስደናቂ የኮሪደር ልማት ተሠርቷል ብለዋል። የወልድያ ከተማን ድብቅ ውበቷን የገለጠ ልማት በመሠራቱ የከተማዋን የሥራ ኀላፊዎች እና ኅብረተሰቡን አመሥግነዋል።

በሁሉም የክልሉ ከተሞች እየተሠራ ያለው ልማት ከተሞች በፈጣን የልማት ግስጋሴ ውስጥ መኾናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።

የከተሞች ልማት የብልጽግና ግስጋሴ አይቀሬ መኾኑን አመላካች መኾኑን ነው የገለጹት። ለዚህ ያበቃን ቁልፉ መነሻ የፓርቲያችን የዕይታ እና የእሳቤ ለወጥ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የልማት ሥራ መሻገሪያ ነው ያሉት ኀላፊው ይህን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

#አሚኮ_ዜና #የኮሪደር_ልማት #ወልድያ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በጤና ምርምር እና ትምሀርት ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ሥራ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚኾን ነው” የጎረቤት ሀገራት የሕክምና ተማሪዎች