
አዲስ አበባ: ሰኔ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የሕክምና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ 400 የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች ያሉ ሲኾን ከእነዚህ መካከል የደቡብ ሱዳን እና የሶማሌ ላንድ የሕክምና ተማሪዎች የተለያዩ የጤና እና የምርምር አንዲሁም የትምህርት ተቋማትን እየጎበኙ ነው።
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን በጋራ ከጎረቤቶቿ ጋር ለመከላከል ቁርጠኛ ናት ያሉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሒ እንዲህ ዓይነት ትምህርቶች እና ጉብኝቶች የጎረቤት ሀገር ዲፕሎማሲን በማሳደግ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በራሷ አቅም የምትበለጽግ፣ በራሷ ልጆች የምታድግ አህጉር የመፍጠር ዕቅድ ትግበራ አንዱ አካል ነውም ነው ያሉት።
ይህ የትምህርት እና የጉብኝት ሥራ አፍሪካ በልጆቿ መተባበር የተሻለ አህጉር ለመፍጠር ያለመ የአጀንዳ 2063 አካል ነው ያሉት የአርማወር ሀንሰን የምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ናቸው።
የምንፈልጋትን አፍሪካ በጤናው ዘርፍ እንገነባለንም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዋናነት የፓን አፍሪካኒዝም አንቀሳቃሽ እንደመኾኗ ለተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች ዕድል መስጠት ትብብር እና ትስስርን ለመፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአርማወር ሀንሰን የምርምር ማዕከል ዘመኑን የሚመጥን በዋናነት 40 የላቦራቶሪ ማዕከላት አሉት።
የላቦራቶሪ ጽዳጅ ማስወገጃ ማዕከል እና ደረቅ ቆሻሻ የሚታከምበት ስፍራም አሉት። ይህም የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች ይህንን ትግበራ በሀገራቸው እንዲኖር ጉብኝቱ ያግዛል ብለዋል።
የሕክምና ተማሪዎቹ ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ትልቅ መኾኑን በመጥቀስ በተለይ አርማወር ሀንሰን የምርምር ማዕከል አንደ አፍሪካ ምሳሌ የሚኾን እና ድንበር አልባ ምርምሮችን ለመሥራት ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #ሕክምና #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
