
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የሰላም፣ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት ከከተማዋና ከክልሉ መሪዎች ጋር ተወያይቷል።
“ባሕር ዳርን ወደ ላቀ ከፍታ ለመውሰድ የወጣቶች ሚና የማይተካ ነው ” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው የውይይት መድረክ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደኾነ ጠቁመዋል።
አሁን ያለው ወጣት ታሪክ ተቀባይ ብቻ ሳይኾን ታሪክ ሠሪም ነው ብለዋል። ይህንንም የባሕር ዳር ከተማ ወጣት በተግባር እንዳሳየ ገልጸዋል። በቀጣይም ወጣቶች የባሕርዳር ከተማ ሰላምን እና አንድነቷን ጠብቀው እንዲያስቀጥሉ ነው የጠየቁት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማዋ ነዋሪ ሚና ከፍተኛ ቢኾንም የወጣቶች ተሳትፎ እና ሚና የላቀ እንደነበር ተናግረዋል። ይህም የባሕር ዳር ከተማ ወጣት ሰላም ወዳድ፣ ለልማት የተነሳሳ፣ ከመንግሥት ጎን የቆመ መኾኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
የዛሬው ምክክርም እንደ ምርጫ ጊዜው መሪው ከወጣቶች ጋር አብሮ ለመወያየት እና አብሮ ለመሥራት ያለመ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ “ሰላምን ጠብቆ ከተማዋን የልማት ተቋዳሽ ለማድረግ ሠርተን በተግባር ያሳየነውን እና ለሕዝባችን የሰጠነውን ተስፋ አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት።
የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶችም በቀጣይ በከተማዋ የሚሠሩ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በማገዝ ሚናቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
#አሚኮ_ዜና #ወጣቶች_ለልማት #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
