
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በዶና በር፣ በልደታ እና በዕውቀት ፋና ትምህርት ቤቶች በ20 ሚሊዩን ብር ያስገነባቸውን አራት ብሎኮች አስመርቋል።
የ8ኛ ክፍል ተማሪ እጹብ ደሳለኝ እና ፈንታነሽ ክንድየ ከግንባታው በፊት ለመማር ማስተማር ምቹ እንዳልነበር ገልጸዋል። የክፍሎቹ መገንባት ሕጻናት ሙሉ ትኩረታቸው ትምህርት ላይ እንዲኾን ያስችላል ነው ያሉት።
ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚኾኑ እያንዳንዳቸው አራት ክፍሎች የያዙ ሦሥት ብሎኮችን ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደገነባ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ግንባታዎቹ በጤና ቢሮ፣ በአማራ መልሶ ማቋቋም ፈንድ እና በፌዴራል ግብርና ኮርፖሬሽኖች ድጋፍ የተገነቡ መኾኑን ተናግረዋል። በክረምት በጎ አድራጎት ሥራ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ከማኅበረሰቡ እና ከተቋማት የሚጠበቅ መኾኑን አሳስበዋል።
.
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንት አደመ የቅድመ አንደኛ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በባሕርዳር ከተማ በመንግሥት እና በእረጅ ተቋማት እየተገነቡ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ወሳኝ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በቅርቡ በፌዴራል መንግሥት እና በክልሉ 308 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ወደ 3 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት ለመገንባት ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) መንግሥት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሮች ቅድሚያ ለትምህርት እንዲሰጡ በማድረግ ጤናማ እና የተማረ ማኅበረሰብ ለማፍራት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
#አሚኮ_ዜና #የትምህርት ቤቶች_ግንባታ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
