
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በወቅታዊ የልማት እና የሰላም ሥራዎች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር በባሕር ዳር ከተማ እየተወያዩ ነው። በመድረኩ የሰላም እና የልማት ሥራዎችን በትጋት በማከናወን ሀገርን ወደ ላቀ ከፍታ ለመውሰድ የወጣቶች ሚና ምን መኾን እንዳለበት ተነስቶ ውይይቶች ተደርገዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት በወጣቶች ሁለንተናዊ እና የነቃ ተሳትፎ ሀገር ይገነባል፤ የሕዝብ ሰላም በዘላቂነት ያረጋገጣል፤ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከዳር ያደርሳል። የባሕር ዳር ከተማ ብሎም የአማራ ክልል ወጣቶች በትላልቅ ሀገራዊ ኹነቶች በንቃት የሚሳተፉ፣ በውጤትም አጅበው ሥራዎችን የሚፈጽሙ ናቸው ብለዋል።
ወጣቶች በተለይም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላሙ የተጠበቀ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበር አንስተው ምሥጋናም አቅርበዋል። ወጣቶች ከመሪዎቻቸው ጋር በመተባበር የልማት ሥራዎችን እያከናወኑ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ለሀገር ከፍታ እየሠሩ ያሉ ወጣቶች ከፍታቸውን የሚመጥን ክብር ይገባቸዋልም ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ። ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ፣ የወጣትነት ጊዜያቸውን እና አቅማቸውን በሙሉ ሥራ ላይ እንዲያውሉ እና የራሳቸውን እና የሀገራቸውን ኢኮኖሚያዊ ልዕልናም እንዲያረጋግጡ እንሠራለን ብለዋል።
“ለሕዝብ ሰላም እና ልማት የሚተጉ ወጣቶች የሀገር መሠረቶች ናቸው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሁሉም ወጣቶች ሀገርን በሚጠቅሙ ዘርፎች ላይ ሁሉ በንቃት በመሳተፍ የልማት አርበኛ መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት እና መሪዎች የወጣቶችን ሕልም ለመደገፍ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።
#አሚኮ_ዜና #ወጣቶች_ለልማት_ባሕር ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
