ልማትን ከኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ጋር አስተሳስሮ በመሥራት ወልድያ ተሞክሮ ኾናለች።

11

 

ወልድያ: ሰኔ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአርባ ከተማዎች ከንቲባዎች እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊዎች ከክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ጋር በመኾን የወልድያ ከተማን ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ተሞክሮዎች ተመልክተዋል።

ሙሽራዋ ወልድያ ከተማም እንግዶቿን በፍቅር ተቀብላ ልማቶቿን አስጎብኝታለች።

የመሶብ አንድ ማዕከል፣ የኮሪደር ልማት ፣የሳይንስ ካፌ እና የባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) የሕዝብ ቤተመጻሕፍት፣ በእንግዶቹ ተጎብኝተዋል።

የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ትውልዱን ከቴክኖሎጂ ጋር ለማላመድ እና አንባቢ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ከተማዋ ሩቅ ህልም እንዳላት አመላካች ነው ብለዋል።

በተለይ የመሶብ አንድ ማዕከል ግምባታ ከሚሴም ለመሥራት ጀምራለች ያሉት ከንቲባው በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዳለብን ከወልድያ ተሞክሮ ቀስመናል ነው ያሉት።

ይህን ሁሉ ወልድያ ድምጿን አጥፍታ መሥራቷም እንዳስደነቃቸው የከሚሴ ከንቲባ አስረድተዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ ከተማ የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተስፋሁን ታደለ ልማትን ከኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ጋር አስተሳስሮ መሥራት አንደሚቻል ከወልድያ ተሞክሮ አይተናል ብለዋል።

አይቻልም እና ሰላም የለም የሚሉ ምክንያቶችን ጥሳ ሕዝቧን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ ልማቶች በከተማዋ መሥራት መቻሉ ለሌሎች ከተሞች መነሳሳትን ይፈጥራል ነው ያሉት።

የደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ወልድያን ከአሁን በፊት አውቃታለሁ አሁን ላይ ዲጂታል ወልድያ ኾና አግኝቻታለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

ትልቁ ነገር ሀሳብ ነው፤ ሀሳብ ላይ ተሠርቷል፤ ዜጎች በከተማዋ ልማት እንዲደሰቱ የሚያደርግ ከኮሪደር ልማት ጎን ለጎን ዘመናዊ የግብይት ማዕከላት ተገንብተዋል፤ ይህም በኮሪደር ልማት የሚነሱ መልሶ ማቋቋም እና የከተማዋ ፍሬ ተቋዳሽ እንዲኾኑ ማድረግን ተሞክሮ ወስደናል ነው ያሉት።

የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው በወልድያ ከተማ በነበረን ጉብኝት ሰው ተኮር ተግባር ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚያስገነዝብ ተሞክሮ ቃኝተናል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን የሚፈታ፣ የከተሞችን የመልካም አሥተዳደር ችግርን የሚቀርፍ የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታ አስደማሚ ነው ብለዋል። ከደብረብርሃን አኳያ የወልድያ ግንባታ በፍጥነት መጠናቀቁ ልዩ ትኩረት እንድንሰጥ ያስገነዘበን ተግባር ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱም ከተለመዱት የእግረኛ መንገድ እና የብሥክሌት መሥመር ባሻገር የሕዝብ መዝናኛ እና መናፈሻዎችን ያካተተ መኾኑ በተሞክሮ ሊወሰድ እንደሚገባውም አስረድተዋል።

#አሚኮ_ዜና #የወልድያ_የኮሪደር_ልማት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

ዘጋቢ:- ካሳሁን ኀይለሚካኤል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመስዋዕትነት የጸና፣ በፈተና ያለፈ፣ ፈተናን የሚሻገር የጸጥታ ኀይል እየገነባን ነው”
Next article“በወልድያ ከተማ የተሠራው ልማት የውበት ብቻ ሳይኾን የኢኮኖሚ እና የትውልድ ግንባታ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)