
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ዘነበ ወልዴ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዝቋላ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት በመሳተፍ በዓመት ከ300 ሺህ ብር በላይ ተጠቃሚ ኾነዋል።
ማንጎ፤ ሙዝ፣ ብርቱካን እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማልማት እና ቤተሰባቸውን በማሥተዳደር የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመኾንም በቅተዋል።
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት 72 ሺህ ኩንታል የፍራፍሬ ምርት መመረቱን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በመምሪያው የአትክልት እና ፍራፍሬ ቡድን መሪ ደሳለኝ አዳነ በአትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
🥑 አቮካዶ፣ ፓፓየ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን እና ሎሚ በብዛት እየተመረተ መኾኑንም ገልጸዋል። በ2018 የምርት ዘመን ከ46 ሺህ ኩንታል በላይ ለማምረት ታቅዶ 72 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቷል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሆርቲ ካልቸር ልማት ተወካይ ዳይሬክተር አወቀ ዘላለም በ2018 የምርት ዘመን በመስኖ እና በመደበኛ የአትክልት ልማት ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
8 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የፍራፍሬ እና 150 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የቡና ምርት መገኘቱንም ተናግረዋል። ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ ልማት ተሸፍኗል ነው ያሉት።
በክልሉ በቋሚነት ከ15 በላይ የፍራፍሬ ዓይነቶች እንደሚለሙም ገልጸዋል።
በመስኖ ድግግሞሽ ልማት ወደ 1 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሲኾኑ በፍራፍሬ ልማት ከ600 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ደግሞ ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይ የፍራፍሬ ልማትን ይበልጥ ለማሳደግ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
#አሚኮ ዜና #ፍራፍሬ ልማት #አማራ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
