
ይህች ቀን ዕለት ብቻ አይደለችም፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከሀዘን ወደ ደስታ፣ ከተስፋ ቢስነት ወደ ተስፋ ልምላሜ፤ ከባይተዋርነት ወደ ሕዝብ አጋርነት የቀየረች ድንቅ ዕለት ናት።
ይህች ዕለት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ እና ኢትዮጵያዊያን ከብሔር ተኮር አቀንቃኝ አገዛዝ፤ የጦርነት አባዜ ከማይለቀው የሕገወጡ ሕወሃት ቡድን አገዛዝ የተላቀቁበት ቀን ነው።
በዚህች ታሪካዊ ዕለት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ከዘር ማጽዳት ዘመቻ እንዲላቀቁ፤ ከሥደት እና መፈናቀል እንዲተርፉ፤ በቋንቋቸው በአደባባይ እንዲናገሩ፤ በባሕል እንዲያጌጡ፤ የነጻነት አየርን እንዲተነፍሱ ከሕገወጡ የሕወሃት አገዛዝ እንዲላቀቁ የምሥራቅ በር የከፈተች ታሪካዊ ዕለት ናት።
አንች ወልቃይት ጠገዴ ሆይ፤ አንች ጠለምት ሆይ እንኳን ደስ ያለሽ፤ እንኳን ብርሃንን ለማየት አበቃሽ፤ እንኳን የነጻነት አየር ተነፈሽ የተባሉበት ቀንም ነው።
👉ከሐምሌ 5/2008 ዓ.ም በፊት:-
ሕገወጡ ሕወሃት በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ታሪክ አዋቂዎች “በባዶ ስድስት” ካምፕ እንዲገደሉ አድርጓል። በርካታ ነዋሪዎች ከአባቶቻቸው ዕርስት እንዲፈናቀሉ፤ እንዲታሠሩ እና እንዲንገላቱ ተደርጓል።
በርካታ የቆሰሉ የሕወሓት ታጣቂዎችን እስከ ቤተሰቦቻቸው፤ በ1977 በድርቅ ምክኒያት ወደ ሱዳን የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች እና ድርቅን መከላከል በሚል ፕሮግራም በርካታ የትግራይ ተወላጆችን በወልቃይት ጠገዴ እንዲሠፍሩ በማድረግ የዴሞክራፊ ቅየራ አድርጓል።
ሕዝቡ ማንነቱን እንዲያጣ፣ በቋንቋው እንዳይናገር፣ ባሕሉን እንዳያራምድ በማድረግ ማንነታቸውን ለማጥፋት ሠርቷል።
ወልቃይቶች ስለ ዕርስታቸው ተዋደቁ፤ በየገደሉ እስከ ሕይወታቸው ተወረወሩ፤ በባዶ ስድስት ካምፕ ሰውነታቸው በጅራፍ ተተለተለ፤ አማርኛ በማውራታቸው የሞት ጽዋን ተጎነጩ።
የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰ፤ ወልቃይቶች ከፋቸው “ከፋኝ” ብለው የበርሃውን ንዳድ ተቋቁመው ለክብራቸው፣ ለነጻነታቸው፣ ለአባቶቻቸው ዕርስት ተዋደቁ። ተዋድቀውም አልቀሩ ሐምሌ አምስትን መነሻ ያደረገው ትግላቸው በኢትዮጵያዊን አጋርነት እና የአብሮ ተጋድሎ የነጻነት ካባ ተጎናጸፉ።
የሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ሥልጣን በኢትዮጵያዊያን አንድነት ተገረሰሰ። ኢትዮጵያም በልጆቿ መስዋዕትነት ነጻ ወጣች። ቡድኑ በሥልጣን ዘመኑ “የግዛት መሥፋፋት፣ የብሔርተኝነት ፖለቲካ እና ኢትዮጵያን ማፈራረስ” ላይ ትኩረት አድርጎ ሢሠራ እንደነበር “የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የታፈኑ እውነታዎች” በሚል በአማራ ክልል በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ትብብር በ2014 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል።
ዛሬ ወልቃይት በልማት ጎዳና ላይ ነች፤ ነጻነታቸውን ተጎናጽፈው ሰላማቸውን አጽንተዋል፤ ከስደት ተመልስው በአንድነት የአባቶቻቸውን ዕርስት እያለሙ ነው። ዳግም ለወረራ የሚመጣን ኀይል በተከዜ ዘብ ሊደመስሱ አፈሙዛቸውን ወልውለው መሳሪያቸውን አንግበው ተከዜ ላይ ጸንተዋል።
በግፉ ብዛት ከሥልጣኑ የወረደው ሕገወጡ ቡድን ዛሬም ሥልጣንን በመቆጣጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነትን አማራጩ አድርጓል።
ለሕገወጡ ቡድን ሰላም ሕመሙ ነው ጦርነት ደግሞ መድኃኒቱ ነው። ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር “ጽምዶ” ብሎ ተቆራኝቷል። የመንግሥትን ሰፊ የሰላም አማራጭ ባለመቀበል ጸንቷል። በትግራይ ወጣቶችን አሥገድዶ በማፈን ወደ ጦር ማሠልጠኛ አሥገብቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በርካታ የትግራይ ወጣቶች በጉልበት እየታፈሱ በሱዳን ጦርነት እንዲሳተፉ፣ ሕይወታቸውን እንዲያጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
መንግሥት በትዕግሥት የሚያየው ከግጭት ቁም ነገር እንደማይገኝ ስለሚያውቅ መኾኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የሰላም መደፍረስ ምንጩን ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና በመፍጠር ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።
መንግሥት የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ነገር ለመከላከል ዝግጁ ነውም ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #ሐምሌ_5 #አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
