በትራምፕ እና በኢራን መካከል ያለው አሁናዊ ውጥረት እና የስምምነት ሚዛን !

20

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን ገልጸዋል። የኢራን ባለሥልጣናት ግን የአጸፋ እርምጃ የመውሰድ ዛቻዎቻቸውን ከዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች ጋር እያጣጣሙ ይገኛሉ።

የአሜሪካ የቃላት ለውጥ የመጣው በኢራን ላይ ሊሰነዘር የነበረው ጥቃት ሊፈጸም ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው በትራምፕ ትዕዛዝ ከተሰረዘ በኋላ ነው። ሁለቱም ወገኖች ታላቅ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ኢራን ኢንተርናሽናል የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ዋቢ በማድረግ አጠናቅሯል።

እንደ አክሲዮስ እና ፖሊቲኮ ዘገባዎች ከኾነ አሁን እየታየ ያለው የመጀመሪያ ደረጃ የመግባቢያ ሰነድ የሆርሙዝ ወሽመጥን ያለ ምንም ክፍያ ወዲያውኑ ለመክፈት፤ የአሜሪካን እገዳ ለማንሳት እና የተኩስ አቁሙን ለ60 ቀናት ለማራዘም ያለመ ነው ተብሏል። የኑክሌር ጉዳዩ ግን ለቀጣይ ምዕራፍ ተትቷል ነው የተባለው።

ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት ገና በይፋ አልተፈረመም፤ አክሲዮስ ሰነዱ የመጨረሻ ማረጋገጫ ያስፈልገዋል ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስንም ብሏል። ይህ የዲፕሎማሲ ጥረት የመጣው ትራምፕ ቀደም ሲል በኢራን የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ካስፈራሩ በኋላ ነው።

የኢራን ወታደራዊ እና የፓርላማ አመራሮች በበኩላቸው የአሜሪካ ጥቃት ከቀጠለ ቀጣናዊ የነዳጅ ገበያው እንደሚናጋ እና አሜሪካም የማያልቅ ቅርቃር ውስጥ እንደምትገባ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

ከተኩስ አቁሙ ጎን ለጎን በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ የድሮን ጥቃቶች መሞከራቸው እና የኢራን ባሕር ኅይል የንግድ መርከቦችን ማገዱ ውጥረቱ አሁንም መቀጠሉን ያሳያል።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት አሜሪካ በወሰደቻቸው ውስን ወታደራዊ እርምጃዎች የሆርሙዝ ወሽመጥን የኢራን ስጋት ለማድረግ እና የሥነ-ልቦና ሚዛኑን ወደ እሷ ለመጠቅለል እየሞከረች ነው። ወታደራዊ ጫናውም የድርድሩ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ትራፕ ግን ስምምነቱን እርግጠኛ ኾነው ተናግረዋል። “ከኢራን ጋር የነበረው ጦርነት አብቅቷል፤ ሀገሪቱም የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት ለመኾን እንደማትጥር ስምምነት ላይ ተደርሷል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የስምምነቱ እጣ ፈንታ የሚወሰነው ትራምፕ “ሊጠናቀቅ ተቃርቧል” ካሉት ይልቅ ቴህራን አሁን እየተደረገባት ያለውን ወታደራዊ ጫና ስምምነቱን ለመፈረም ወይስ አቋሟን ይበልጥ ለማጠንከር ትጠቀምበታለች ወይ በሚለው ላይ ይኾናል።

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጤና መረጃዎች ላይ ምን ያህል ይጠነቀቃሉ?
Next article🏭 ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ከስኳር ምርት ባሻገር !