በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጤና መረጃዎች ላይ ምን ያህል ይጠነቀቃሉ?

13

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበራዊ ሚዲያ ዋነኛ የመረጃ መለዋወጫ መንገድ ኾኗል። መረጃን አጣርቶ የሚጠቀመውን መውሰድ ደግሞ ግዴታ ነው።

በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የጤና መረጃዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል። ምክኒያቱ ደግሞ መረጃዎች ሲተላለፉ የሚታዩ ክፍተቶች እና ሊከተሉ የሚችሉ የጤና አደጋዎች አሳሳቢ በመኾናቸው ነው።

የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር መኮንን አይችሉህም
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጤና መረጃዎችን ከመተግበር በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።

✍️በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ ሲተላለፍ በመረጃ ሰጭው እና በተቀባዩ መካከል ግልጽ የኾነ መስተጋብር ሊኖር ይገባል። ይኹን እንጂ አኹን ባለው ኹኔታ የሚለቀቁ መረጃዎችን አጣርቶ የመረዳት እና የመጠቀም ልምዱ ዝቅተኛ እንደኾነ ነው የገለጹት።

✍️በአብዛኛው የሚሠራጩ የጤና መረጃዎች ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከባሕላዊ እውቀት ያልዘለሉ እና የተጋነኑ በመኾናቸው በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ ነው ያሉት።

✍️ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች መድረኩን ለንግድ ዓላማ ብቻ ሲለጠቀሙበት ይታያል። እነዚህ አካላት የሕክምና ተግባራትን እጅግ አጋነው በማቅረብ ኅብረተሰቡን ባልተገባ መንገድ ለመሳብ ይሞክራሉ።

✍️ይህ አይነቱ የተጋነነ ማስታወቂያ የሕክምና ሥነ ምግባርን የሚጥስ ነው። ከዚህ በላይ ሰዎች ትክክለኛውን የሕክምና አማራጭ እንዳያገኙ እና ለከፋ የጤና ቀውስ እንዲዳረጉ ያደርጋል።

✍️የጤና መረጃዎች በንግድ ፍላጎት እና በተጋነነ ኹኔታ መቅረባቸው ኅብረተሰቡ በጤናው ዘርፍ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸርም ያደርጋል ብለዋል ዶክተር መኮንን።

✍️ምን ይደረግ?

#ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገኛቸውን የጤና መረጃዎች ሳያረጋግጥ ከመቀበል ይልቅ የመረጃውን ትክክለኛነት ማወቅ እና ፈቃድ ካላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ወይም ተቋማት ማረጋገጥ ለጤና ዋስትና ነው።

#በማኅበራዊ ሚዲያ የሚታዩትን ነገር ሁሉ በራስ ላይ ከመሞከር በፊት
የመረጃውን ምንጭ እና የመረጃ ሰጭውን ማንነት መመርመር እና በአካል ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም መክረዋል።

#በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጤና መረጃዎች እና ማስታወቂያዎችም ሙያዊ መርሕን የተከተሉ እንዲኾኑ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ አለበት ባይ ናቸው።

✍️ሲጠቃለል፦

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የጤና መረጃዎች ለትምህርት ሊጠቅሙ ይችላሉ። ካልተጣሩ ግን እስከ ሞት ድረስ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

መረጃዎችን በጥንቃቄ መመርመር፣ ባለሙያዎች ሥነ ምግባርን መጠበቅ እና መንግሥት የቁጥጥር ሥራውን ማጠናከር የጤና ቀውስን ለመከላከል ወሳኝ መፍትሄዎች መኾናቸውን ነው ዶክተር መኮንን ያነሱት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበገጠር መንገድ ተደራሽነት ከ49 በላይ ወረዳዎችን እርስ በእርስ ለማገናኘት እየተሠራ ነው ።
Next articleበትራምፕ እና በኢራን መካከል ያለው አሁናዊ ውጥረት እና የስምምነት ሚዛን !