በገጠር መንገድ ተደራሽነት ከ49 በላይ ወረዳዎችን እርስ በእርስ ለማገናኘት እየተሠራ ነው ።

16

 

​ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በክልሉ የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት እና ነባር መንገዶችን በመጠገን ኅብረተሰቡ ያልተቋረጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠራ ይገኛል። የኤጀንሲው ዋና ሥራ አሥኪያጅ ቀለሙ ሙሉነህ በ2018 በጀት ዓመት የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው በ33 ፕሮጀክቶች አማካይነት 102 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ እና ከ227 በላይ ስትራክቸሮችን ለመገንባት አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል። ከእነዚህም ስድስቱ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንደኾኑ ነው የተናገሩት።

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ከ49 በላይ ወረዳዎች እርስ በእርስ ከማገናኘታቸውም በላይ ለዞኖች ትስስርም ትልቅ ፋይዳ አላቸው ነው ያሉት።

ከመንገድ ግንባታዎች ጎን ለጎን ነባር መንገዶችን ለክረምት ምቹ የማድረግ ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ አስቀድሞ 6 ሺህ 2 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ 289 የመንገድ መስመሮችን ለመጠገን ታቅዶ እስካሁን 78 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። በክረምት ድንገተኛ የመንገድ መስተጓጎሎችን በፍጥነት ለመፍታት ልዩ የጥገና መርሐግብር ተዘጋጅቷልም ነው ያሉት።

​የመንገድ ልማት ማኅበራዊ ትስስርን ከመፍጠር ባለፈ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማነቃቃት የሕዝቡን የዕለት ከዕለት ኑሮ ለማሻሻል ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል። በቀጣይ የክልሉን የ25 ዓመት የዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ መሠረት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ይገባሉ ነው ያሉት።

​የጸጥታ ችግር በሥራው ተግዳሮት ቢኾንም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት። ሕዝቡም ለመንገድ ልማቱ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት ።

መንገዶቹን ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቃቸው እና እንዲንከባከባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ_ዜና #የመንገድ_መሠረተ_ልማት_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጡረተኞች ያላቸውን የሕይወት ልምድ እና ዕውቀት ለሀገር ዕድገት እና ለሰላም ግንባታ ሊጠቀሙት ይገባል።
Next articleበማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጤና መረጃዎች ላይ ምን ያህል ይጠነቀቃሉ?