
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ጡረተኞች አርዓያ የጡረተኞች በጎ አድራጎት ማኅበር ጡረተኞች ያካበቱትን ሰፊ ልምድ እና ዕውቀት በመጠቀም በኢኮኖሚ፣ በልማት እና በሰላም ግንባታ ሂደቶች ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር የምስረታ ጉባኤ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አበራሽ ታደሰ ፤ ጡረተኞችን በጡረታ አበል ብቻ ከመወሰን ይልቅ በራሳቸው ጥረት ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደገፍ እና ማበረታት ይገባል ብለዋል።
ባካበቱት ልምድ እና ጥበብ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያላቸውን አቅም መጠቀም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአርዓያ የጡረተኞች በጎ አድራጎት ማኅበር ሊቀ መንበር አቃኔ አድማሴ የማኅበሩ ዓላማ ጡረተኞች በቤታቸው የሚውሉበትን ሁኔታ በመቀየር፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር አቅማቸውን ወደ ሥራ እንዲቀይሩ ማድረግ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ማኅበሩ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ከመንግሥት ጥገኝነት በመውጣት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል።
የማኅበሩ አባል አቶ ተረፈ አለሙ ልማት እና ትውልድን ማስቀጠል፤ መሥራት እና መለወጥ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ለሰላም በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ጡረተኞች ልማትን ለማፋጠን ብሎም ዕውነትን እና ሀቅን መሠረት ያደረገ ትውልድ ለመፍጠር የመምከር ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሌላኛዋ የማኅበሩ አባል ወይዘሮ ሙሉጎጃም ኃይሌ ጡረታ መውጣት የሥራ ፍጻሜ ሳይኾን፣ ጡረተኞች ያላቸውን ዕውቀት እና ጉልበት ተጠቅመው ራሳቸውን በኢኮኖሚ መገንባት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል። በተለይ ከጠባቂነት ወጥቶ ራስን መቻል ለሌሎች አርዓያ መኾን ይገባል ነው ያሉት።
ማኅበሩ የጡረተኞችን የሰው ሀብት ለሀገር ግንባታ በማዋል፣ የትውልድ ቅብብሎሽን ለማረጋገጥ እና ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ ጠንክሮ እንደሚሠራም ተገልጿል።
#አሚኮ_ዜና #ጡረተኞችን_ለልማት_ባሕር_ዳር_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
