“ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘግቡ ሀገራት ቀዳሚ መኾን ችላለች” አቶ አሕመድ ሽዴ

10

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 25ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ለ 2019 ዓ.ም የፌዴራል ረቂቅ በጀት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከፍተኛ እድገትን አስመዝግቧል ነው ያሉት። ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ኢኮኖሚው የ6 ነጥብ 8 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ የ9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት መመዝገቡን የገለጹት ሚኒስትሩ በ2018 ዓ.ም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ መተንበዩንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የተቀናጀ የገንዘብ እና የፊዚካል ፖሊሲዎችን በመተግበር በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት ቀዳሚ መኾን መቻሏንም ገልጸዋል።

ለዚህ እድገት እየተተገበረ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የግብር ገቢ ማሻሻያ፣ የበጀት ጉድለት ምጣኔ መቀነስ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለረጅም ጊዜ የሚያሳድጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉ ለእድገቱ መመዝገብ ምክንያቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እና የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የ2019 ዓ.ም የፌዴራል በጀት ታሳቢ ተደርጎ መቅረቡን አብራርተዋል።

በጀቱ የተመደበላቸው ክልሎች እና ተቋማት ለታለመለት ዓላማ በቁጠባ እና በአግባቡ እንዲጠቀሙም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የቀረበውን ረቂቅ በጀት መነሻ በማድረግ የምክር ቤት አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎች እና ሀሳቦችን አንስተዋል።

የ2019 ረቂቅ በጀት ለተጨማሪ ዝርዝር ዕይታ ለፕላን ልማት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

ዘጋቢ: ቤተልሔም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባ ተመድ አሳሰበ።
Next articleጡረተኞች ያላቸውን የሕይወት ልምድ እና ዕውቀት ለሀገር ዕድገት እና ለሰላም ግንባታ ሊጠቀሙት ይገባል።