“የደብረ ማርቆስ ከተማ የሰላም ችግሩን ቀልብሳ ልማት ላይ ትገኛለች”

5

 

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ነገ የሚመረቀውን የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት የአውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ታላላቅ የልማት ሥራዎች አሉ ነው ያሉት።

የልማት ሥራዎቹ የከተማዋን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የከተማዋን እድገት የሚያፋጥኑ መኾናቸውን ተናግረዋል። የልማት ሥራዎቹ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው ብለዋል። ዛሬ የተጎበኙት የልማት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ያሉ እና ግንባታቸውን አጠናቅቀው አገልግሎት መጀመር ብቻ የሚቀራቸው እንደኾኑም ገልጸዋል።

ደብረ ማርቆስ ለልማት ምቹ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ይሄን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል። ከተማዋ በጽንፈኛ ኃይሎች የተፈጠረውን የሰላም ችግር ቀልብሳ የልማት ሥራዎችን መሥራቷን ነው የተናገሩት። ከተማዋ አሁን ሰላማዊ መኾኗንም ገልጸዋል።

ዛሬ ከተጎበኙት በተጨማሪ 253 የኢንዱስትሪ ፕሮጄክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። እየተሠሩት ያሉት የልማት ሥራዎች ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት ከአካባቢው ርቀው የነበሩ ባለሀብቶች ወደ ከተማ ተመልሰው እንዲያለሙ ጠይቀዋል። በከተማዋ ለሥራ የተመቸ ሰላም እንዳለም አስታውቀዋል።

ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ካላት ጸጋ አንጻር በበቂ ሁኔታ አለመልማቷንም ተናግረዋል። በከተማዋ እና በጠቅላላው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለኢንቨስትመንት የተመቸ እምቅ ጸጋ አለ፤ በዙህ ጸጋ ልክ ከተማዋን ማልማት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

አዲስ የተገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ ለከተማዋ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም እንደሚኾን ገልጸዋል። ከተማዋ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሌሎች ዘርፎች የተመቸች መኾኗን ተናግረዋል።

በቀጣይ የከተማዋን የኮሪደር ልማት እንደሚያሰፉ እና የኢንዱስትሪ ፍሰትን እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል።

በተሠሩት የልማት ሥራዎች የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበርም አንስተዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ለልማት ቀናኢ ናቸው ብለዋል። የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ይዘን ታላላቅ ሥራዎችን እንሠራለን ነው ያሉት።

#ደብረ_ማርቆስ #የልማት_ሥራዎች #ኢንቨስትመንት #የኮሪደር_ልማት #አውሮፕላን_ማረፊያ #አሚኮ #DebreMarkos #AmharaRegion
#አሚኮ #ባሕር_ዳር #ሐምሌ4_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።