የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባ ተመድ አሳሰበ።

9

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ላይ ያነጣጠረ የተጠናከረ የጥቃት ማዕበል ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ አጠናክራ መቀጠሏን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል።

ጥቃቱ የተሰነዘረው በሆርሙዝ የውኃ መስመር ላይ የአሜሪካ ሄሊኮፕተር መውደቋን ተከትሎ ነው። ይህም ሁለቱ ወገኖች በሰኔ ወር ካደረጉት የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲህ የተመዘገበው እጅግ አስከፊው የስምምነት መፍረስ ኾኗል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የስምምነቱ መፍረስ ቀጣናዊ ውጥረቱን እያባባሰው መኾኑን አስጠንቅቀዋል። ሰፊ ቀውስ እንዳይከሰትም ሁሉም ወገኖች ወደ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እንዲመለሱ አሳስበዋል።

በሁለቱም ወገኖች ጥቃቶች ቢሰነዘሩም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገው ድርድር አሁንም መቀጠሉን ዘጋርዲያን የተለያዩ መገናኛ ብዙኀንን ዘገባ ዋቢ በማድረግ ያጠናክራል።

ሲኤንኤን እንደዘገበው ደግሞ ሌሊቱን ሙሉ ከተካሄደው ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረጉት ንግግሮች በጥሩ መስመር ላይ ይገኛሉ።

ሮይተርስ በበኩሉ ተደራዳሪዎች የታገዱ የኢራን ገንዘቦችን መልቀቅ ስለሚቻልበት አሠራር እየተወያዩ መኾኑን ገልጿል። ኢራን የታገደባት ከ6 እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንዲለቀቅላት ትፈልጋለች። ዋሽንግተን ግን ገንዘቡ ለሰብአዊ ቁሳቁሶች ግዥ ብቻ በደረጃ እንዲለቀቅ ትፈልጋለች፤ በቀጥታ የመመለሱን ሃሳብም ውድቅ ታደርጋለች።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካን የቅርብ ጊዜ ጥቃት አጥብቆ ኮንኗል። ጥቃቶቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና የሀገራትን ሉዓላዊነት የጣሱ መኾናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል። ድርጊቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱንም በተግባር ትርጉም አልባ እንዳደረገው አስታውቋል።

#አሚኮ_ዜና #አሜሪካ_ኢራን_ድርድር

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልል ተቋማትም ወደ ዲጂታል አሠራር መግባት አለባቸው” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)