
አዲስ አበባ: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በዲጂታላይዜሽን የትግበራ ሂደቶች ላይ በርካታ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው ሀገሪቱ በ2030 የምታልመውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
“የሰውን ሕይወት ከውልደት እስከ ሞት የያዙ ወሳኝ ሰነዶችን ወደ ዲጂታል የማዘመን ሥራ እጅግ ወሳኝ ነው” ያሉት ዶክተር በለጠ ሞላ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ከወረቀት አሠራር ወጥተው ወደ ዲጂታል አሠራር መሸጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ይህ የዲጂታላይዜሽን ሂደት የአገልግሎት አሰጣጥን ከማቀላጠፉ ባሻገር፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር እንደሚያመጣ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
“ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን ስንል በሁሉም የሀገሪቱ ተቋማት ላይ ያሉ ሰነዶችን ቀስ በቀስ ሀገራዊ መልክ በማስያዝ ነው” ብለዋል።
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እየተከናወኑ ያሉትን የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል። ሚኒስትሩ ተቋሙ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
ይህ ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን ሁሉንም ክልሎች ወደ ዘመናዊ አሠራር ማስገባት እንደሚገባ እና ይህም ለዲጂታል 2030 ስትራቴጂ መፈጸም ቁልፍ ነገር መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ በበኩላቸው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያስችሉ አስፈላጊ ማሽኖች እና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተከላ መጠናቀቁን ገልጸው አዲሱ የሲቪል ምዝገባ አገልግሎት ትግበራ የአሠራር ግልጽነትን በመፍጠር ሌብነት እና ብልሹ አሠራርን ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር መኾኑን ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ከውልደት እስከ ሞት ያሉ ማኅበራዊ ሁነቶችን ሰንዶ የሚይዝ በመኾኑ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ በወረቀት ተመዝግበው የቆዩ ታሪካዊ መረጃዎችን ወደ ዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓት የማዘመን ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ይህንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግም ብቁ ባለሙያዎች ተሰማርተው እየሠሩ መኾኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
#አሚኮ_ዜና #የዲጅታል_ሥራ_በአዲስ_አበባ_ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
