
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሳቢ አበራ ፋንታሁን የአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91.4 ሬዲዮ ጣቢያን ጎብኝተዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሁሉም አካባቢዎች እና ሚዲያ መጠነ-ሰፊ ተደራሽነት ያለው ተቋም መኾኑን ጠቅሰዋል።
አሚኮ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ቅርንጫፎቹን በማስፋት የሕዝብ ድምጽ ኾኖ ማኅበረሰቡን እያነቃ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ተቋሙ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እየተወጣ ያለው ኀላፊነት የላቀ መኾኑን የገለጹት አቶ አበራ አሚኮ የፀጥታ ችግር ሳይበግረው ሕዝብ እና መንግሥትን በድልድይነት እያገናኘ ያለ የአማራ ክልል ምልክት መኾኑን አስገንዝበዋል።
ተቋሙ እና የተቋሙ አባላት በጽኑ ተቋማዊ እሴት የተገነቡ በመኾናቸው ለዚህ ተግባራቸው የክልሉ ምክር ቤት ልዩ ክብር እና ዕውቅና መስጠቱንም አስታውሰዋል።
የአማራ ኤፍ ኤም ደብረ ብርሃን 91 ነጥብ 4 ሬዲዮ ጣቢያ ላለፉት 12 ዓመታት ለደብረ ብርሃን፣ ለሰሜን ሸዋ እና ለአጎራባች አካባቢዎች የሚዲያ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን ሠብሣቢው አንስተዋል።
ጣቢያው ሰፊ ሥራዎችን በውስን የሰው ኀይል እና ሀብት እያከናወነ እንደሚገኝም በጉብኝታቸው ወቅት ተመልክተዋል።
በቀጣይም ጣቢያው በአደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ ከዘመኑ ጋር አብሮ እንዲዘምን ምክር ቤቱ የቤት ሥራ መውሰዱን አቶ አበራ አረጋግጠዋል።
ምክር ቤቱ ለጣቢያው ዕድገት ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እንደሚወጣም አስታውቀዋል።
አሚኮ በተለያዩ አካባቢዎች ትላልቅ የሚዲያ ተቋማትን እየገነባ በመኾኑ በቀጣይም በደብረ ብርሃን ተመሳሳይ ግንባታ እንዲያከናውን ምክር ቤቱ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #አሚኮ_ደብረ_ብርሃን_ኤፍ_ኤም_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
